የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ በሚያካሂደው ሕዝበ ውሣኔ፤ የመራጮች ትምህርት በመስጠት ከሚሠማሩ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ምክክር እና የስልጠና መድረክ አካሄደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኅዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም ከሲቪል ማኅበራቱ ጋር ያደረገውን ምክክር በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ውብሸት አየለ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ሕዝበ ውሣኔው በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ላይ ድምፅ በመስጠት ለመሣተፍ ቅድመ ሁኔታውን የሚያሟሉ ዜጎች በነፃነትና በሰላማዊ መንገድ ፍላጎታቸውን የሚገልጹበትን ዲሞክራሲያዊ የምርጫ ዐውድ ለማረጋገጥ እንዲቻል ቦርዱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ እንደሚገኝና በዕለቱም በመራጮች ትምህርት ላይ ከተሠማሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር የሚካሄደው ምክክር የዚሁ አንድ አካል እንደሆነ ተናግረዋል። የቦርድ አመራር አባል የሆኑት አበራ ደገፉ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዜጎች በንቃት እንዲሣተፉና ፍላጎታቸውንም በነፃነት እንዲገልጹ ማሰተማር አሰፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እና ቦርዱ እንዳዲስ ከተቋቋመ በኋላ በተካሄዱት ሁለቱ ሕዝበ ውሣኔዎች ላይ የሲቪል ማኅበራቱ እና የትምህርት ተቋማት የነበራቸው ሚና የላቀ እንደነበር አስታውሰዋል።
ቦርዱ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች ላይ ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሣኔ የመራጮች ትምህርት ለመስጠት ፍላጎት ላላቸው የሲቪል ማኅበራት ያደረገውን ጥሪ ተከትለው ላመለከቱና መሥፈርቱን አማልተው የተገኙ 29 የሲቪል ማኅበራትና የትምህርት ተቋማት ከቦርዱ ፍቃድ አግኝተው ሥራቸውን ከወዲሁ እንደ’ጀመሩ አበራ (ዶ/ር) ተናግረዋል። የቦርድ አመራሩን ንግግር ተከትሎ በቦርዱ የሲቪክና የመራጮች ትምህርት የሥራ ክፍል ኃላፊው አወያይነት የሥራ ክፍሉ ትኩረት የሚያደርግባቸው የመራጮች ትምህርት ዋና ዋና ባህሪያት፣ የትምህርቱን አስፈላጊነትና በማን ሊሰጥ እንደሚገባ፣ ትምህርቱን በመስጠት የሚሠማሩ ተቋማት የፍቃድ አሰጣጥ ሂደት፣ የቦርዱ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ያላቸው ኃላፊነትና ሥልጣን፣ የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ ባለሞያዎች የሚሠጡ ሥልጠናዎች፣ የመራጮች ትምህርት በመስጠት ላይ የተሠማሩ ተቋማት ሊከተሏቸው የሚገቡ የሥነ-ምግባር ደንቦች፣ የማኅበራቱን ዐቅምና የገንዘብ ምንጭ በተመለከተ፣ እንዲሁም የሕዝበ ውሣኔን ባህሪያትና ቦርዱ በቀጣይ ለማካሄድ በእንቅስቃሴ ላይ ያለው ሕዝብ ውሣኔ ልዩ ባህሪያትን አስመልክቶ ውይይት ተደርጓል።
በተጨማሪም ቦርዱ የመራጮች ትምህርትን አፈጻጸም የሚቆጣጠርበት አግባብነትና የሚከተላቸው የቁጥጥር ሥርዓት፣ የመራጮች ትምህርቱን በሕጉ በተጣለባቸው የኃላፊነት ደረጃ በማይፈጽሙ ተቋማት ላይ ሊወሰዱ የሚችሉ የዕርምት ‘ርምጃዎች፣ የሲቪል ማኅበራቱ ከቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጋር ሊኖራቸው የሚችለው የሥራ ግንኙነት ወሠንና የሪፖርት አቀራረብን የተመለከተ ገለጻ ለተሣታፊዎቹ የተደረገ ሲሆን፤ በማስከተልም መድረኩ ለተሣታፊዎች ክፍት ተደርጎ ሃሳብ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ተደርጓል። ከተሣታፊዎች በተሰጡ አስተያየቶችም፤ የመራጮች ትምህርት የሚሰጡ ባለሞያዎች ሥምሪት ከቦታ ቦታ ተመጣጣኝ አለመሆን የሚፈጥረው ክፍተት፣ ከቦርዱ የተሰጣቸውን የዕውቅና ደብዳቤ እያሳዩም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በፀጥታ አካላት “ከበላይ አካል አልተነገረንም” በሚል ምክንያት መጉላላት እንደሚገጥማቸው፣ የፋይናንስ ውሥንነትና የፀጥታ ሥጋት ያለባቸው አካባቢዎች ተግዳሮት እንደሆኑባቸው ገልጸዋል። የእለቱ ሁለተኛ መድረክ የሆነው የሥርዓተ ፆታና አካታችነት ጉዳይም በሁለት ክፍሎች የቀረበ ሲሆን፡ በመጀመሪያው ክፍል፡ የቦርዱ የሥርዓተ ፆታና አካታችነት ሥራ ክፍል ኃላፊ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ገለፃ ሰጥተዋል፦ በመጪው ህዝበ ውሳኔ ቦርዱ ትኩረት የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተሳታፊ ያደረገ ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ እያደረገ ያለውን ዝግጅት፡ ቦርዱ ባለፉ ጊዜያት ባካሄዳቸው የምርጫ እንቅስቃሴዎች ላይ የታዩ ስርዐተ ፆታ እና ማህበራዊ አካታችነትን የተመለከቱ ጉዳዮችን ለማስተካከል የወሰዳቸው እርምጃዎች እና የስርዓተ ጾታ እኩልነት እና የማህበራዊ አካታችነት ፅንሰ-ሀሳቦች በህዝበ ውሳኔው የመራጮች ትምህርት ተካታች ማድረግ የሚቻለባቸውን መንገዶች ነው።
በሁለተኛው ክፍል ለተሳታፊዎች ስልጠና የተሰጠ ሲሆን፡ ስልጠናው አሳታፊ በሆነ መልኩ ሶስት አይነት የማቅረቢያ መንገዶችን፡ የቡድን ስራ፡ በጥያቄ እና መልስ እና በተለምዶ የማስተማር ሂደቶችን በመጠቀም ተሰጥቷል። በስልጠናው ክፍለ ጊዜ ቀርበው ውይይት ከተደረገባቸው አርእስት መካከል፡ በህዝበ ውሳኔ ሂደት ውስጥ ለአካታችነትና ሥርዓተ ጾታ ጉዳይ የተለየ ትኩረት መስጠት የሚያስፈልግባቸው ምክንያቶች፡ የሴቶች፡ ወጣቶች፡ የአካል ጉዳተኞች፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችና ህዳጣን (አነስተኛ ቁጥር ተናጋሪዎች ያላቸው ቋንቋዎች ማህበረሰቦች) በህዝበ ውሳኔ ተሳትፎ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ሁኔታዎች፡ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን ለመቋቋም መወሰድ የሚችሉ እርምጃዎች፡ በህዝበ ውሳኔ በመራጭነት መሳተፍ ትኩረት ለሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚያስገኛቸው ፖለቲካዊ ጥቅሞች፡ የማግለል ጉዳቶች፡ የማካተት ጥቅሞች፡ አካታች የመራጮች ትምህርት አሰጣጥ መልካም ተሞክሮዎች፡ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ማህበረሰቦች ውስጥ ስለሚገኙ ዜጎች እና በህዝበ ውሳኔ መሳተፍ ጉዳያቸው የማይመስላቸውን ማግኘት የሚሉት ናቸው።
አካታችነትን አስመልክቶ ከተሣታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ፡ የሚስተዋሉ የሥርዓተ-ፆታ ልዩነቶች፣ ማህበራዊ ጫና እና አመለካከቶች ለሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ጉልህ እንቅፋት እንደሆኑ፣ አካል ጉዳተኞች ህዳጣን እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በ ዲሞክራሲ ሂደቶች ውስጥ ለመሳተፍ በሚያደርጉት ጥረት፡ መገለል እና ማህበራዊ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሟቸው፡ የተሳትፎ የእድሎች እጦት እንዲሁም የእውቀት እና የመረጃ እጥረት የሚሉት ይገኙበታል። የሲቪል ማህበራት ተወካዮቹ ለመድረስ አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎችን እንዲሁም በቋንቋ አነስተኛ የሆኑ የማህበረሰብ አካላትን ያካተተ የመራጮች ትምህርት ለመስጠት በሚያደርጉት ጥረት ሊያጋጥማቸው የሚችሉ ተግዳሮቶች በርካታ እንደሚሆኑ ካለፈ ልምዳቸው በመነሳት ገልፀው፡ በዋናነት፡ የፀጥታ ችግሮች እንደሚያሰጋቸው እና የአቅም እጥረት የማስተማር ተግባራቸውን ሊገድብ እንደሚችል ገልፀዋል።
ከውይይቱ በኋላም የቀረቡት የመፍትሄ ሃሳቦች ከሴቶች እና ከተገለሉ ቡድኖች ጋር ብቻ ሳይሆን በአካባቢያቸው ካሉ እንዲሁም በማህበረሰቡ ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱትን ውሳኔ ሰጪ አካላት እንዲሁም አስተያየት መሪዎች ስለአካታችነት አስፈላጊነት ማስተማር፤ እውቀትን እና መረጃን ስኬታማ በሆነ መልክ እና መጠን ለማስተላለፍ ከተመሳሳይ ማህበረሰብ የመጡ ሰዎችን መጠቀም፣ የአካታችነትን ግንዛቤ መፍጠር፤ የሚዲያ መልእክቶችን እና የገጽ ለገጽ ስልጠና በመጠቀም አናሳ ቡድኖች የሚያጋጥሟቸውን መገለሎች ለመፍታት ማስተማር እና ከህብረተሰቡ ጋር መስራት፤ እንዲሁም ለሥርዓተ-ፆታ ትኩረት የሚሰጡ መረጃዎችን መዝግቦ መያዝ ናቸው፡፡ ለቀረቡት ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ግብረ መልስ የተሰጠባቸው ሲሆን የእለቱን የውይይት መድረክ የቦርዱ አመራር አበራ ደገፋ (ዶ/ር) መዝግያ ንግግር በማድረግ ቋጭተውታል፡፡