የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል በሚገኙ 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች ላይ ለሚያካሂደው ሕዝበ ውሣኔ የተፈፀሙ ዋና ተግባራት
የዕቅድና በጀት ዝግጅት
- ህዝበ ውሣኔውን የሚካሄድባቸውን ቦታዎች እና ምርጫ ጣቢያዎችን በመለየት፣ መረጃዎችን በማሰባሰብ እና በማደራጀት ቦርዱ ዝርዝር ዕቅድ አዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አቅርቧል። (መስከረም 10 ቀን 2015 ዓ.ም)
- የህዝበ ውሳኔውን ለማስፈጸም ከተጠየቀው በጀት ብር 541 ,270,104.82 (አምስት መቶ አርባ አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሰባ ሺ አንድ መቶ አራት ብር ከሰማኒያ ሁለት ሳንቲም) ውስጥ 410,100,000 (አራት መቶ አስር ሚሊዮን አንድ መቶ ሺ) ተፈቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። (ጥቅምት 1 ቀን 2015 ዓ/ም)
- በቀጣይም ተጨማሪ በጀት የሚያስፈልጋቸውን ዝርዝር ተግባራት አዘጋጅቶ ያቀርባል።
የህዝበ ውሳኔ ጽ/ቤቶችን ማደራጀት
- ለሕዝብ ውሳኔው አፈፃፀም የሚያስፈልጉ ጽ/ቤቶች እንዲከፈቱ ቦርዱ ለስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳ መስተዳድሮች በደብዳቤ መስከረም 9 ቀን 2015 ዓ/ም በመጻፍ አሳውቋል።
- የቢሮዎቹን ሁኔታ ለመመልከት 6 የዞን እና 2 ልዩ ወረዳዎች እንዲሁም 22 የማስተባበሪያ ጽ/ቤት በቦርድ ሰብሳቢ፣በቦርድ አባላት እና በባለሙያዎች የመስክ ጉብኝት ተደርጓል።
- በአርባ ምንጭ ከተማ የሕዝበ ውሳኔ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት እና ፣ በስድስት ዞኖች እና በአምስት ልዩ ወረዳዎች ቢሮ እና መጋዘን እንዲሁም በ25 የህዝበ ውሳኔ ማእከላት ቢሮዎች እና መጋዘኖች ለሕዝበ ውሣኔው ዝግጁ ሆነዋል።
- የአንዳንድ የህዝበ ውሳኔ ቢሮዎች መጠነኛ ዕድሳት፣ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ እና የቢሮ ቁሳቁስ የሚቀራው ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል።
የምርጫ ጣቢያ ማደራጀት
- የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በተመዘገበው የመራጭ ቁጥር ላይ 10% ተጨማሪ ማስተማመኛ ቁጥር በመውሰድ ለሕዝበ ውሣኔው በስድስት ዞኖችና በአምስት ልዩ ወረዳዎች 3,751 ምርጫ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ ቦርዱ ወስኖ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል። http://nebe-elections.org.et/pslist
የተፈናቃይ ጣቢያዎችን ማደራጀት
- ሕዝበ ውሳኔ በሚካሄድባቸው ቦታዎች የሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎች በሕዝበ ውሣኔው እንዲሣተፉ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት አማካኝነት መረጃ የማሰባሰብ ስራ ተከናውኗል።
- ከክልሉ መንግሥት በተገኘው መረጃ መሠረት በኮንሶ፣ በደራሼ፣ በአማሮ እና በአሌ ልዩ ወረዳዎች ላይ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ 10,075 ተፈናቃዮች የሚገኙ ሲሆን 18 ምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን ለመመዝገብ እና ድምፅ ለማስጠት ተፈናቃዮቹ በሚገኙበት ካምፕ ለማደራጀት የሚያሰችል እቅድ እየተዘጋጀ ይገኛል።
የሕዝበ ውሣኔ ሀላፊዎች እና አስፈጻሚዎች ምደባ/ምልመላ
- በህዝበ ውሳኔው ዋና ጽ/ቤት ደረጃ አፈፃፀሙን የሚመራ አምስት አባላት ያሉት ቡድን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።
- ለ6 ዞን እና 5 ልዩ ወረዳዎች ህ/ውሳኔ ጽ/ቤቶች ከዚህ በፊት በዞን አስተባባሪነት እና በምርጫ ክልል አስፈጻሚነት ያገለገሉ፣ በስራ አፈፃፀም የተሻሉ 33 አስፈጻሚዎች ተመርጠዋል።
- በ25 የሕዝበ ውሳኔ ማዕከላት(sub units) በዞን እና በምርጫ ጣቢያ መካከል ሆነው የሎጀሰቲክስ እና የኦፕሬሸን ሥራዎችን የሚሰሩ 156 አስፈጻሚዎች ተመርጠው ለህዝበ ውሳኔ ዝግጁ ሆነዋል።
- በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የተሣተፉ ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑ፣ የትምህርት ዝግጅታቸው ከ12ኛ ከፍል በላይ የሆኑ፣ (ሴት የምርጫ አስፈጻሚዎችን በማበረታት ማስታወቂያ ወጥቶ) በ3,751 ምርጫ ጣቢያዎች የሚያገለግሉ 18,755 የምርጫ አስፈጻሚዎች ተመልምለዋል::
- 27, 854 የምርጫ አስፈጻሚዎች በ3,584 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተደለደሉ ሲሆን በ 167 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ አስፈጻሚዎች ያላመለከቱ በመሆኑ ለእነዚህ ጣቢያዎች ድጋሚ ማስታወቂያ ወጥቷል። https://pollworkers.nebe-elections.org/recruitment
የባለድርሻዎች ተሳትፎ
- ቦርዱ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ከመንግሥት አካላት ጋር በጊዜ ሠሌዳ እና የህዝበ ውሳኔ የኦፕሬሽናል ዕቅድን በተመለከተ በአራት መድረኮች ውይይት አደርጓል።
- ህዝበ ውሳኔው በሚካሄድባቸው ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ያሉ የፀጥታ ሁኔታን ክትትል በማድረግ ዝርዝር የፀጥታ ሁኔታ ትንተና አድርጓል።
የሠነዶች ህትምት እና የቁሳቀስ ግዢ
- ለህዝበ ውሳኔው ማስፈጸሚያ የህትምት እና የቁሳቁስ የግዢ አገልግሎት ለማግኘት በሀገር ውስጥ ጨረታ በማውጣት ጥረት የተደረገ ሲሆን ነገር ግን ከጊዜ እና ከዋጋ ጋር በማናጻፀር ከግዢ ኤጀንሲ ፍቃድ በማግኘት ከአጋር በተገኘ የውጪ ሀገር የግዢ አገልግሎት እንዲፈጸም ተደርጓል።
- ህትመትን በተመለከተ ከሀገር ውሰጥ አሳታሚ ድርጅት የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እና ፎርሞች ለማሳተም የተገኘው ግምት ቫትን ጨምሮ ብር 156,718,697.18 የኢትዮጵያ ብር ሲሆን ይህም ወደ 2.8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ ነው። ሆኖም ግን ከዚህ በፊት የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን ካቀረበው አልጉራይ ከተባለው ድርጅት የተገኘው ለህትመት የሚያስፈልግ የገንዘብ መጠን ደግሞ ከዱባይ አዲስ አበባ የአየር ትንስፖርትን ጨምሮ 612, 926 .14 የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡ ስለሆነም በሁለቱ መሀል ንጽጽር ሲሰራ በሀገር ውስጥ ማሳተሙ ከ4 እጥፍ በላይ የገንዘብ ብልጫ እንዳለው ማየት ተችሏል፡፡
- የውጪ የግዢ አገልግሎት የተከናወነው ከዚህ በፊት በ6ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ የግዢ አገልግሎቱን ከሰጠአጋር ድርጅት ማለትም ከተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት /ዩኤንዲፒ/ ጋር በመተባበርር ሲሆን ሂደቱም ሎጀስቲክስ
- ከፌዴራል ፖሊስ በመነጋገር የማዕከል መጋዘን በቂ ጥበቃ እንዲኖረው ተደርጓል፡፡
- ለ31 ማዕከላት የመራጮች ምዝገባ ሰነድ እና ቁሳቁሶችን አጅበው የሚሄዱ የፌዴራል ፖሊስ አባለት ምደባ እዲጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል።
- ስፋቱ 2200 ካሬ ሜትር የሆነ የ ቁሳቁስ ማከማቻ እና መደልደያ መጋዘን በኪራይ የአገልግሎት ግዢ ተፈጽሞ ለስራው አመቺ እንዲሆን ተደርጔል፡፡
- ከውጭ ሀገር የታዘዙ የስልጠና ፣ የምዝገባ እና የድምጽ አሰጣጥ ሰነድ እና ቁሳቁሶች የመረከብ ስራ ተሰርቷል።
- የመራጮች ምዝገባ የስልጠና ሰነዶችን ድልደላ/packing/ እየተካሔደ ይገኛል፡፡
- ለመራጮች ምዝገባ በሰማያዊ ሳጥን ውስጥ የሚታሸጉ የመራጮች መዝገብ ፣ ስድስት የመራጮች ካርድ ፣ የእስቴሽነሪ ኪት እና ፣ ቅጾች ከ 1 – 9 ለድልድል ተዘጋጅተዋል።
- የስርጭት እቅድ እና አጭር ስልጠና ለዞን አስተዳደር ኃላፊዎች ተሰጥቷል፡፡
የህዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ሰነድ(Concept of Operations)
- ሁሉንም የህዝበውሳኔ ሂደቶችን (processes) በግልፅ የሚያስቀምጥ፤የህዝበ ውሳኔው አስፈፃሚዎች የሚያከናውኑትን ተግባራት እና ሀላፊነታቸውን የሚዘረዝር፤የተጠያቂነት፣ የመረጃ ልውውጥ ፣ የስራ ግንኙነቶች እና የሪፖርት መስመሮችን የሚያሳይ ሰነድ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።
የድምጽ መስጫ ወረቀት ምልክት መረጣ
- በድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ የሚቀመጥ ምልክትና ስያሜ እንዲያሳውቁ ለ6 ዞኖች እና 5 ልዩ ወረዳዎች በደብዳቤ ተገልጾላቸው ነጭ እርግብ መርጠው ለቦርዱ አሳውቀዋል።
ስልጠና
- የሕዝብ ውሳኔ አስፈጻሚዎችን በተገቢው መንገድ ለማሠልጠን እንዲያመች የመራጮች ምዝገባ ማኑዋል ተሠርቶ ለኅትመት ተዘጋጅታል።
- 31 ማዕከላትም የሥልጠና ቦታ ለስልጠና ዝግጁ ሆነዋል።
- በስልጠናው የሚሰማሩ የፊልድ አሰልጣኞች ምልመላ ተጠናቋል።
የሕዝበ ውሳኔ ዘገባ ፍቃድ
- ሕዝበ ውሣኔውን ለመዘገብ ፍላጎት ላላቸው መገናኛ ብዙኃን አካላት በቦርዱ የማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ አማካኝነት ጥሪ ተደርጓል።
- ይህ ሪፖርት እስከተጠናከረበት ጊዜ አምስት መገናኛ ብዙኃን ማመልከቻቸውን አስገብተዋል።
- የዘገባ ዕውቅና ለተሰጣቸው ጋዜጠኞች የሚሰጠው ሥልጠና ዕቅድ ተነድፎ ተጠናቋል።
የመራጮች ትምህርት
- ለ29 የሲቪል ማህበራት የመራጭ ትምህርት ለመስጠት እውቅና ተሰጥቷል እውቅና የተሰጣቸው ማህበራት ለስራቸው የሚረዳለስራቸው አጋዥ የሚሆኑ ግብዓቶች እንዲደርሳቸው እየተደረገ ነው፡፡
- ከአካታችነት የስራ ክፍል ጋር በመሆን በመጪው ህዳር 27 ለሁሉም የሲቪል ማህበራት የምክክር መድረክ ተዘጋጅቷል፡፡
- ለህዝበ ውሳኔው ተከራካሪዎች እና ለክርክር አዘጋጆች ጥሪ በማስተላላፍ ከ10 ተከራካሪዎች እና ከሶስት የክርክር አዘጋጆች የፍላጎት መግለጫ ተቀብሏል::
- ቦርዱ የመራጮች መረጃ መስጠትን በተመለከተ ያለበትን ግዴታ ለመወጣት ለህዝብ አገልግሎት ማስታወቂያ ስክሪፕት ጽሁፍ ተጠናቆ የፕሮዳከሽን ስራ ተጀምሯል፡፡
ትኩረት የሚሹ ዜጎችን በተመለከተ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች፡
- የህዝበ ውሳኔ አስፈፃሚዎች ምልመላው ፍትሃዊ የፆታ ተዋፅኦን ባማከለ መልኩ እንዲከናወን ተደርጓል።
- የህዝበ ውሳኔው አፈፃፀም ትኩረት የሚሹ ዜጎችን ተሳትፎ ባረጋገጠ ሁኔታ እንዲከወን ማጣቀሻ ሰነድ ተዘጋጅቶ በስራ ላይ ውሏል።
- የህዝበ ውሳኔ አስፈፃሚዎችን ትኩረት የሚሹ የማህበረሰብ አባላትን ልዩ ፍላጎቶች ባማከለ መልኩ ማሳተፍ እንዲችሉ ለማሰልጠን ራሱን የቻለ ማኑዋል ተዘጋጅቷል።
- የህዝበ ውሳኔ አስፈፃሚዎች ትኩረት የሚሹ የማህበረሰብ አባላትን ባማከለ መልኩ ማሳተፍ እንዲችሉ የመረጃ ቋት ታትሞ ለስርጭት ቀርቧል።
- በምዝገባም ሆነ ድምፅ አሰጣጥ ወቅት፡ ሴቶች፡ ወጣቶች፡ አካል ጉዳተኞች፡ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንዲሁም ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች በተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያበረታቱ የሚዲያ መልእክቶች አካባቢ በሚነገሩ ቋንቋዎች እየተዘጋጁ ይገኛሉ።
- የህዝብ አገልግሎት የሚዲያ መልእክቶች እንዲሁም የማህበራዊ አካታችነት የሚዲያ መልእክቶች በምልክት ቋንቋ ተተርጉመው እንዲቀርቡ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
ታዛቢዎችን በተመለከተ
- ከኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ (አይ ሲቲ) ክፍል ጋር በመተባበር በማኑዋል የነበረውን ምዝገባ የሚያስቀር አዲስ የምዝገባ አፕልኬሽን በማልማት እና ወደስራ በማስገባት ህዝበ ውሳኔውን ለመታዘብ የሚፈልጉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በኦን ላይን ምዝገባቸውን አንዲያከናውኑ ማድረግ ተችሏል::
- የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ በኦን ላይን ምዝገባቸውን ሲያደርጉ ያጋጠማቸውን ችገሮች ለማስወገድ እንዲረዳ በቦርዱ የአይቲ ባለሞያዎች የግማሽ ቀን ገለፃ እንዲያገኙ ተደርጓል ::
- የታዛቢነት እውቅና ለሚሰጣቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መርጠው ለሚልካቸው ተወካዮቻቸው የአንድ ቀን ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቋል::
- የሲቪል መህበራት ድርጅቶቹን ወክለው በታዛቢነት ለሚሰማሩ የመስክ ታዘቢዎችና አስተባባሪዎቻቸው የሚያስፈልገው የባጅ ዲዘይን ስራ፤ የህትመት ስራ ዝግጅት ተከናውኗል ::
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ኅዳር 21 ቀን 2015 ዓ.ም.