Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ፓርቲዎች ያካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔን ተከትሎ ውሣኔዎች አሣለፈ

ሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሞዴፓ) ላይ

የተወሠነበት ቀን ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም.

መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም በቁጥር ሞዴ82/2014 በተፃፈ ደብዳቤ ፓርቲው መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ በሚመለከት ሪፖርት አቅርቧል።

ቦርዱ ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ፓርቲው ከሪፖርቱ ጋር አያይዞ ያቀረባቸውን ሠነዶች ከሕጉ፣ ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ እና የቦርዱ ታዛቢዎች ካቀረቡት ሪፖርት አንጻር መርምሯል።

I. አግባብነት ያላቸው የዐዋጁ አንቀጾች ተፈጻሚ የሚሆኑባቸው ጉዳዮች፡-

ሀ/ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 17(1) “ጠቅላላ ጉባዔው 200 ተወካዮች ይኖሩታል፡፡” የሚለው እና በአንቀጽ 62(3) መሠረት ምልዓተ-ጉባዔው 101 መሆኑ ከዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 74(1)(ሰ) ጋር የሚቃረን በመሆኑ አግባብነት ያላቸው የዐዋጁ አንቀጾች ተፈጻሚ እንደሚሆኑ፤ በቀጣይ ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ አስፈላጊው ማስተካከያ ተደርጎበት እንዲቀርብ፤

ለ/ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 17(3) ላይ ጠቅላላ ጉባዔው ለሦስት ወራት ሊራዘም ይችላል የሚለው ከዐዋጅ ቁ. 1162/2011 አንቀፅ 74(1)(ሸ) ጋር የሚቃረን በመሆኑ አግባብነት ያላቸው የዐዋጁ አንቀጾች ተፈጻሚ እንደሚሆኑ፤ በቀጣይ ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ አስፈላጊው ማስተካከያ ተደርጎበት እንዲቀርብ፤

II. በፓርቲው ቀጣይ ጠቅላላ ጉባዔ መፅደቅ ያለባቸው የደንብ ማሻሻያዎች

ሐ/ በደንቡ አንቀጽ 18(1) ላይ በድምፅ የሚካፈሉ የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ብዛት በአስፈጻሚ ምክር ቤት ይወሠናል የሚለው ቢያንስ ከ402 መብለጥ ያለበት በመሆኑ ተሣጻሚ እንዳይሆን እና በቀጣይ ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ አስፈላጊው ማስተካከያ ተደርጎበት እንዲቀርብ፤ መ/ በደንቡ አንቀጽ 19(4) ላይ “መዋቅር ያደራጃል፣ ያጥፋል፣ ያሻሽላል” የሚለው መዋቅሮቹ በደንቡ ከተዘረዘሩት ውጪ ስለመሆናቸው ወይም በግልጽ ካልተዘረዘሩ ለአፈጻጸም አስቸጋሪ ስለሆነ ተፈጻሚ እንዳይሆን እና በቀጣይ ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ አስፈላጊው ማስተካከያ ተደርጎበት እንዲቀርብ፤

ሠ/ በደንቡ አንቀጽ 31 (13) “ሥራውን በአግባቡ አልተወጣም ብሎ ካመነ” የተባለው የትኛው የፓርቲውን አካል እንደሆነ በግልጽ ያልተቀመጠ በመሆኑ ተፈጻሚ እንዳይሆን እና በቀጣይ ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ አስፈላጊው ማስተካከያ ተደርጎበት እንዲቀርብ፤

ረ/ 1162/2011 አንቀጽ 74(3) የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ የፓርቲው “አመራሮችና” በየደረጃው ያሉ “ኃላፊዎች“ አመራረጥ ግልጽ፥ ነፃና ፍትሐዊ እንዲሁም በሚሥጢር በሚሰጥ ድምፅ መንገድ የሚመረጡ መሆናቸውን መደንገግ አለበት ስለሚል የደንቡ አንቀጽ 62(3) “በምሥጢር በሚሰጥ ድምፅ” የሚል ማካተት ያለበት በመሆኑ ተፈጻሚ እንዳይሆን እና በቀጣይ ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ አስፈላጊው ማስተካከያ ተደርጎበት እንዲቀርብ፤

ሰ/ የፓርቲው አባላት ለሀገር ዐቀፍና በየደረጃው ላሉ ሀገራዊ ምርጫዎች የሚታጩበት ሥርዓትን በሚመለከት የደንቡ 21(6) እና 45(2) ስለሚቃረኑ ተፈጻሚ እንዳይሆን እና በቀጣይ ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ አስፈላጊው ማስተካከያ ተደርጎበት እንዲቀርብ፤

ረ/ በአባላት ግዴታ ሥር 5(2) (“ተ” ወይም “ነ”-የመጨረሻዎቹ ሁለት ንዑስ አንቀጾች) አባሉ ግዴታውን አልተወጣም በሚል በ6(4) መሠረት አባልነት ማቋረጥ መቻሉ የአባላትን መብት በእጅጉ ስለሚጎዳ ተፈጻሚ እንዳይሆንና ከመተዳደሪያ ደንቡ በማውጣት እንዲያቀርብ፤

ሰ/ አለመግባባቶች ስለሚፈቱበት ሁኔታ በመተዳደሪያ ደንቡ ውስጥ ተካትቶ ስላልቀረበ በቀጣይ ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ እንዲካተት ተደርጎ እንዲቀርብ፣

III. በሰባት ቀናት ውስጥ ማለትም እስከ ሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ መቅረብ ያለበት

• በደንቡ አንቀጽ 21 ላይ “የሥራ አስፈፃሚ ሥልጣንና ተግባር” የሚለው “የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሥልጣንና ተግባር” በሚል ቢስተካከል እና በርካታ “የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ” ለማለት “የሥራ አስፈጻሚ” የሚሉ ተመሳሳይ ግድፈቶች ስላሉ በቀጣይ ጠቅላላ ቋንቋው ታርሞ እንዲቀርብ ቦርዱ ወሥኗል፡፡

በመሆኑም ፓርቲው ከላይ በተገለጸው መሠረት ከዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 ጋር የሚቃረኑ የደንቡ አንቀጾች ተፈጸሚ እንደማይሆኑ አውቆ በዚሁ መሠረት እንዲፈጸም፤ እና የዐዋጁ አንቀጾች ተፈጻሚ እንደሚሆኑ፤ እንዲሁም ፓርቲው በቀጣይ በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርጎ እንዲያቀረብ፤ በተጨማሪም በአንቀጾቹ ላይ ያለውን የቋንቋ ዕርማት በሚመለከት እስከ ሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ አስተካክሎ እንዲያቀርብ ቦርዱ እያሳወቀ ፓርቲው መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ እና ያስተላለፋቸውን ውሣኔዎች የመዘገበ መሆኑን በአክብሮት እንገልጻለን።

አርጎባ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አብዴን) ላይ

የተወሠነበት ቀን ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም.

መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም በቁጥር አብዴን መ-2/085/014 በተጻፈ ደብዳቤ መጋቢት 08 ቀን 2014 ዓ.ም. ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ በሚመለከት ሪፖርት አቅርቧል።

ቦርዱ ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ፓርቲው ከሪፖርቱ ጋር አያይዞ ያቀረባቸውን ሠነዶች ከሕጉ፣ ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ እና የቦርዱ ታዛቢዎች ካቀረቡት ሪፖርት አንጻር መርምሯል።

የመተዳደሪያ ደንቡን በተመለከተ

ሀ/ ተሻሽሏል ተብሎ የቀረበው መተዳደሪያ ደንብ የተሻሻሉትን ድንጋጌዎች ብቻ በመያዙ ለአሠራር ምቹ እና ወጥ ባለመሆኑ የተሻሻሉት ድንጋጌዎች ካልተሻሻሉት ድንጋጌዎች ጋር ተጠቃለው ያልቀረቡ መሆኑ፤

ለ/ አንቀጽ 1 (3) ሥር ጠቅላላ ጉባዔ የወሠነው የውኽደት ጥያቄ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚከለስበት አካሄድ የዐዋጁን አንቀጽ 91 (3)(ሀ) የሚቃረን መሆኑ ታይቷል፡፡

በመሆኑም፡-

1ኛ/ በተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 1(3) የዐዋጁን አንቀጽ 91(3)(ሀ) የሚቃረን በመሆኑ ይህ የመተዳደሪያ ደንብ ድንጋጌ ተፈጻሚ እንዳይሆን፤

2ኛ/ የተሻሻሉት የመተዳደሪያ ደንቡ ድንጋጌዎች ካልተሻሻሉት ድንጋጌዎች ጋር ተጠቃለው በሙሉ የተሻሻለ መተዳደሪያ ደንብ በሰባት ቀናት እስከ ሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲያቀርቡ እና ይህ ሲፈጸም ፓርቲው ያደረገው ጠቅላላ ጉባዔ እና ያስተላለፋቸው ውሣኔዎች እንዲመዘገብ ቦርዱ በዐዋጁ መሠረት ወሥኗል፡፡

ኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ላይ

የተወሠነበት ቀን ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም.

ሚያዚያ 19 ቀን 2014 ዓ.ም በቁጥር ኢሐአፓ/00/2014 በተጻፈ ደብዳቤ ሚያዚያ 1 እና 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ በሚመለከት ሪፖርት አቅርቧል።

ቦርዱ ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ፓርቲው ከሪፖርቱ ጋር አያይዞ ያቀረባቸውን ሠነዶች ከሕጉ፣ ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ እና የቦርዱ ታዛቢዎች ካቀረቡት ሪፖርት አንጻር መርምሯል፡፡

የመተዳደሪያ ደንቡን በተመለከተ

ሀ/ አንቀጽ 27(3)(ሰ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውኽደት እና ግንባር የመፍጠር ውሣኔ ይሰጣል የሚለው ከዐዋጁ አንቀጽ 91(3)(ሀ)፣ 93(2)(ሀ) ጋር የሚቃረን መሆኑ፤

ለ/ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሥራ ዘመን ያልተገለጸ መሆኑ፤

ሐ/ የአባልነት መዋጮ ዓይነትና አከፋፈል በዐዋጁ አንቀጽ 74(1)(መ) መሠረት ያልተገለጸ መሆኑ፤

መ/ የተሻሻለ መተዳደሪያ ደንብ ገፅ 24 አንቀጽ 34 (8) ቀጥሎ ያለ ድንጋጌ የተዘለለ መሆኑን ቦርዱ ተመልክቷል፤

በመሆኑም ቦርዱ በዐዋጁ መሠረት የሚከተሉትን ወሥኗል፡-

1. የተሻሻለ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 27(3)(ሰ) ከዐዋጁ አንቀጽ 91(3)(ሀ) እና 93(2)(ሀ) ጋር የሚቃረን በመሆኑ ይህ የመተዳደሪያ ደንብ ድንጋጌ ተፈጻሚ እንዳይሆን ቦርዱ የወሠነ መሆኑን፤

2. በቀጣይ በሚኖረው ጠቅላላ ጉባዓ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሥራ ዘመን በግልጽ ተለይቶ በመተዳደሪያ ደንብ ተሻሽሎ እንዲካተት፤

3. በቀጣይ በሚኖረው ጠቅላላ ጉባዔ የአባልነት መዋጮ ዓይነትና አከፋፈልን በተመለከተ በመተዳደሪያ ደንብ ተሻሽሎ እንዲካተት፤

የተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ ገጽ 24 ላይ የተጓደሉ ድንጋጌዎች ተሟልተው በሁለት ቀን ውስጥ እስከ ሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲቀርቡ እና ይህ ሲፈጸም ፓርቲው ያደረገው ጠቅላላ ጉባዔ እና ያስተላለፋቸው ውሣኔዎች እንዲመዘገብ ቦርዱ ውሣኔ ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ.ም.

Share this post