መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ድምጽ አሰጣጥ ተከናውኖባቸው በአቤቱታ ምክንያት ይፋ ያልተደረጉ የምርጫ ክልሎችን አስመልክቶ የተሰጠ መረጃ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሶማሌ፣ በሃረሪ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ድምጽ አሰጣጥን በመስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ያከናወነ ሲሆን በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች የአቤቱታዎች ዝርዝር ታይቶ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ይፋ ያልተደረጉ የምርጫ ክልሎች እንደነበሩ ይታወቃል። ቦርዱ የነበሩ አቤቱታዎችን በዝርዝር በማየት በምርጫ ክልሎቹ የተከናውነው የድምጽ አሰጣጥ እና ቆጠራ ላይ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል።
ሶማሌ ክልል
ሙሎሙልቄ ምርጫ ክልል (የክልል ምክር ቤት) - በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ላይ በመዝገብ ላይ የፈረሙ መራጮች እና በሳጥን ውስጥ በተገኙ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እና ወድቀው በተገኙ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች መካከል፣ እንዲሁም ለምርጫ ክልሉ በደረሰው አጠቃላይ የድምጽ መስጫ ወረቀት እና በድምጽ መስጫ ሳጥን ውስጥ እና ከሳጥን ውጪ ካለው ጋር ሲነጻጸር ሊታለፍ (tolerate ሊደረግ) የማይችል የቁጥር ልዩነት በመገኘቱ፣ የድጋሚ ቆጠራ እንዲከናወን የወሰነ ሲሆን በምርጫ ክልሉ የተወዳደሩ ፓርቲዎች እና የግል እጩዎች በድጋሚ ቆጠራውን የሚታዘቡ ወኪሎች እንዲልኩ ጥሪ ተደርጎላቸዋል።
ጅጅጋ ከተማ የምርጫ ክልል (የክልል ምክር ቤት) - 26 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ለአንድ ፓርቲ ድምጽ እንዲሰጥ ተደርጓል የሚለው በብዙ ምስክሮች በመረጋገጡ፣ 13 የምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎች መታዘብ አለመቻላቸው በመረጋገጡ ይህም ከውጤቱ ድምር ጋር ሲታይ ውጤት የሚቀይር መሆኑ ስለታመነበት ቦርዱ የድጋሚ ምርጫ እንዲከናወን ወስኗል
ደ/ብ/ብ/ህ/ክ
በሌሞ 01 የምርጫ ክልል ( የተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት) - የቀረቡትን አቤቱታዎች መራጮች ላይ ወከባ እና ማስፈራራት፤ ወኪሎች እንዳይታዘቡ ከጣቢያ ማባረር፤ መስፈርት የማያሟሉ መራጮች ድምጽ እንዲሰጡ ማድረግ፤ መራጮች በምርጫ አስፈጻሚዎች ጫና እየተደረገባቸው መሆኑ፤ የምርጫ ሚስጥራዊነት አለመጠበቅ፤ የመሳሰሉት ሲሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምርጫ ጣቢያዎች ላይ እነዚህ ጥሰቶች መፈጸማቸው ምስክርነት በመቀረቡ ምርጫው እንዲደገም ቦርዱ ወስኗል።
ምስቃን እና ማረቆ 2 (የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት) - ሚሊሻ ምርጫ ጣቢያ አከባቢ ማስፈራራት፣ መራጭ እንዳይሳተፍ ማድረግ፣ የመራጭ ቁጥር እና ካርድ የወሰደ ቁጥር አለመጣጣም፣ ህፃናት እንዲመርጡ ማድረግ፣ የአመራር ቤተሰብ በየጣቢያው ታዛቢና መራጭ ማስፈራራት፣ አመራሮች ደጋግመው መምረጥ፣ ከምርጫ ማግስት ግለሰቦችን ከመንግስት ስራ ማገድ፣ የህ/ተ/ም እጩ እስራት መፈፀም፣ ፓርቲ አባላትና ታዛቢዎች ላይ ማስፈራራት፣ በምርጫው ቀን ከግማሽ ቀን በኋላ በተፈጠረ ግጭት መራጮች የፈለጉትን መምረጥ እንዳልቻሉ፣ ታዛቢዎች ህይወታቸው ስጋት ላይ በመውደቁ ምክንያት በፖሊስ እርዳታ ጭምር ከምርጫ ጣቢያ መውጣታቸው የቀረቡ አቤቲታዎች ሲሆኑ እነዚህ አቤቱታዊች በአብዛኛው በምስክር እና በማስረጃ በመረጋገጣቸ ፣ በምስቃና ማረቆ 02 ምርጫ ክልል ላይ በምርጫ ቀን በአብዛኛው ምርጫ ጣቢያ ድምጽ ሰጨዎችን የሚያስገድድ የሀይል ተግባር የነበረ መሆኑ በማስረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ የድጋሚ ምርጫ እንዲከናወን ወስኗል፡፡ የምስቃንና ማረቆ 2 የምርጫ ክልል በድጋሚ ምርጫ የተደረገበት ሲሆን ቦርዱ የድጋሚ ምርጫ ሲወስን ይህ ሁለተኛው ነው።