Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሀገር ዐቀፍ ምርጫውን አስመልክቶ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ውይይት አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሐምሌ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ሀገር ዐቀፍ ምርጫውን አስመልክቶ ቀዳሚ መግለጫ ካወጡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ውይይት አካሄደ። አምስቱም የቦርድ አመራሮች፣ የቦርዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚና ሁሉም የቦርዱ የሥራ ክፍል ተወካዮች የተገኙበትን የውይይት መድረክ በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ማኅበራቱ ለምርጫው ስኬታማነት የነበራቸውን አስተዋጽዖ ገልጸው አመስግነዋል። አንድን ምርጫ ተመልካች እንዲኖረው ከሚያደርጉት አካላት ውስጥ ሲቪል ማኅበራት ተጠቃሽ እንደሆኑና ሀገር ዐቀፍ ምርጫውን አስመልክቶም ያቀረቡት ቀዳሚ መግለጫ እንዲሁም በቀጣይም የሚያወጡት መግለጫ ለምርጫ ሂደት መሻሻል ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለዋል። ምርጫ በባህሪው በየጊዜ መሻሻል የሚጠይቅ ሂደት እንደሆነ የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ዜጎች ስለምርጫ የሚኖራቸውን መረዳት ከፍ ማድረግና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችም ምርጫ ሲደርስ ብቻ ሊሆኑ እንደማይገባ አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።

የቦርድ ሰብሳቢዋን ንግግር ተከትሎ ሲቪል ማኅበራቱ በቡድን ተከፋፍለው ሀገር ዐቀፍ ምርጫው ላይ ስለታዘቡት አጠቃላይ ሁነት የተወያዩ ሲሆን፤ የውይይታቸውንም ጭብጥ በቡድን ተወካይ አማካኝነት ለመድረኩ አቅርበዋል። የምርጫ ቅስቀሳው ሰላማዊነት፣ ባለድርሻ አካላትና ፓለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርዱ ላይ ያሳደሩት ዕምነት፣ በቦርዱ የተሠሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ የአካታችነት ሥራዎች፣ የተሰጡ ሥልጠናዎች እና ሕጎችን የማዘመን ሥራ በጥንካሬነት ከተጠቀሱት ውስጥ ሲገኙ፤ በአንጻሩ የታዛቢነት ባጆች በጊዜ ያለመድረስ፤ በምርጫ ክርክር ወቅት የምልክት ቋንቋን ያለመጠቀም እና ማኅበራቱ የሚፈለገውን ያህል በጀት መፍጠር ያለመቻላቸው ከተጠቀሱት ውሥንነቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

የቦርድ አመራር አባል በሆኑት ብዙወርቅ ከተተ ጋባዥነት፤ የቦርዱ የሥራ ክፍሎች አጠቃላይ የሥራ ሂደቶች ላይ እና በማኅበራቱ የቀረቡ ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ የቦርድ አመራሮችን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይም እንዲሁም በቦርድ አመራሮች ማብራሪያ ተሰጥቶበት በቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ የመዝጊያ ንግግር ተደርጎ የመድረኩ ማብቂያ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

Share this post