6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ሂደት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም መከናወኑ ይታወሳል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በእለቱ የፓለቲካ ፓርቲዎች አቤቱታ ዴስክ በማቋቋም በስልክ፣ በአጭር መልእክት፣ በደብዳቤ አቤቱታዎችን ሲቀበል እና በእለቱ መፈታት የሚችሉትን ችግሮችም ሲፈታ መቆየቱ ይታወሳል።>/p>

ቦርዱ ከድምፅ መስጫው ቀን በማስከተል በተለያየ ሁኔታ የቀረቡትን አቤቱታዎች ሲመለከት እና ሲመረምር ቆይቷል። አንዳንዶቹ አቤቱታዎች በየደረጃው በሚከናወነው የምርጫ ሂደት መቅረብ የነበረባቸው እና በምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ደረጃ የሚቀርቡ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ቦርዱ በምርመራ የሚያያቸው ናቸው። ቦርዱ ከአቤቱታዎቹ የተቆራረጡ፣ ሙሉ መረጃ ያልያዙ እና መካተት የሚገባውን መረጃዎች ያካተቱ ባለመሆናቸው ምርመራውን አስቸጋሪ መሆኑን ተረድቷል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስካሁን የቀረቡ አቤቱታዎች ላይ ማጣራቶችን እያከናወነ ቢሆንም በምርጫው የተወዳደሩ እና በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ፣ በውጤት ቆጠራ እና አገላለጽ ላይ አቤቱታ ያላቸው ፓርቲዎች ያላቸውን አቤቱታ (እስካሁን የቀረበውን ጨምሮ) በአንድ አጠቃልለው እና የሚከተሉትን ፍሬ ነገሮች እንዲያሟላ አድርገው በሁለት ቀናት ውስጥ ለቦርዱ እንዲያስገቡ በጥብቅ እያሳሰብን ቦርዱ ቅዳሜን እና እሁድንም እንደሚሰራ ለመግለጽ እንወዳለን።

አቤቱታ ሊቀርብባቸው የሚችሉ ጉዳዮች

ድምፅ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ

  • መስፈርት የሚያሟሉ መራጮች እንዳይመርጡ ተከልክለዋል፣
  • መስፈርት የማያሟሉ መራጮች ድምፅ እንዳይሰጡ ብንቃወምም መደበኛ ድምፅ እንዲሰጡ ተደርጓል
  • መራጮች አንድን የፖለቲካ ፓርቲ ወይም እጩ እንዲመርጡ ተገድደዋል፣
  • መራጮች የፈለጉትን ፓርቲ ወይም እጩ እንዳይመርጡ ገደብ እየተጣለባቸው ነው፣
  • መራጮች በምርጫ አስፈጻሚዎች ጫና እአየተደረገባቸው ነው፣
  • የምርጫው ሚስጥራዊነት ተጠብቆ ድምፅ የመስጠት ሂደት እየተከናወነ አይደለም፣
  • ለመራጮች መደለያ እየተሰጠ ነው፤
  • ምርጫ አስፈፃሚዎች መደለያ እየተቀበሉ ነው
  • የምርጫ ጣቢያው ሕጋዊ ባልሆኑ ሰዎች ቁጥጥር ስር ወድቋል፣
  • ታዛቢዎች እና የእጩ ወኪሎች የድምፅ አሰጣጡን ሂደት እንዳይታዘቡ ተከልክለዋል፣
  • ሀሰተኛ የምርጫ ሰነዶች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው፣
  • የምርጫውን ውጤት የሚጎዳ ሀሰተኛ መረጃ በመሰራጨት ላይ ይገኛል… እና የመሳሰሉት

ከድምፅ ቆጠራና ማዳመር ሂደት ጋር የተያያዘ

  • በህግ መሰረት ዋጋ አልባ የሆኑ እና ጥቅም ላይ ያልዋሉ ወይም የተበላሹ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች በመቆጠር ላይ ናቸው ፣
  • ህጋዊ ድምጽ አላግባብ ዋጋ አልባ እንዲሆን እተደረገ ነው፣
  • የድምጽ መቆጠሩ እና ማዳመሩ ወቅቱን እና ሥርዓቱን ጠብቆ አለመከናወኑ የውጤቱን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል፣
  • የድምጽ መስጫ ሳጥን እሽግ ተቀድዷል፣ ተሰብሯል ወይም ብልሽት ደርሶበታል፣
  • ለምርጫ ጣቢያው ከደረሰው የድምጽ መስጫ ወረቀት ብዛት በላይ የሆነ የድምጽ መስጫ ወረቀት ተገኝቷል፣
  • የድምጽ ቆጠራው እተከናወነ ያለው በሕግ ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ነው፣
  • የድምጽ ቆጠራው በቂ የተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ ብርሃን በሌለበት እንዲከናወን እየተደረገ ነው፤
  • የድምጽ ቆጠራው ሲከናወን ታዛቢዎች፣ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት ወይም የእጩ ወኪሎች እንዳይገኙ ተከልክለዋል ….. እና የመሳሰሉት

ውጤት ይፋ ማድረግን የሚመለከት

  • የምርጫው ውጤት ለህዝብ እስከአሁን ይፋ አልተደረገም አላግባብ እንዲዘገይ እየተደረገ ነው፣
  • የምርጫ ጣቢያ ሀላፊው ለግል እጩ ወይም ለፖለቲካ ፓርቲ ወኪል የውጤት መተማመኛ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም ፣
  • የምርጫ ውጤት መግለጫ ቅጾች በአግባቡ እየተሞሉና እየተፈረሙ አይደለም…. እና የመሳሰሉት ሊሆኑ ይችላሉ።
  • 2/ የአቤቱታ ይዘት: የድምፅ አሰጣጥ፥ ቆጠራ እና ውጤት አገላለፅን በሚመለከት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚቀርብ አቤቱታ በሶስት ቅጂ ተዘጋጅቶ የሚከተሉትን በማካተት በአቤቱታ አቅራቢው ወይም በወኪሉ ተፈርሞ መቅረብ አለበት፡፡
  • አቤቱታው የተፃፈበት ቀን
  • የአቤቱታ አቅራቢው ፓርቲ ሙሉ ስም፣ አድራሻ፣ ሞባይል ቁጥር፣ ኢ-ሜይል፣
  • ለአቤቱታው መነሻ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ፣ ይህም ምክንያቱን ከመግለፅ በተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮችን ማካተት የሚገባው ሲሆን በተለይ የድምፅ አሰጣጥ፥ ቆጠራ እና ውጤት አገላለፅ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የምርጫ ህጎችን ጥስት የተመለከቱ መሆን ይገባቸዋል በተጨማሪም ጥሰቱ የተፈፀመበትን ቦታ/ ምርጫ ጣቢያ፣ምርጫ ክልል/፤ ቀን እና ሰዓት እና ጥሰቱን የፈፀመውን አካል አካቶ ሊይዝ ይገባል
  • አቤቱታ አቅራቢው እየተጠየቀ ያለውን መፍትሄ በተለይ ማመልከት አለበት
  • የማስረጃ ዝርዝር፣ ይህ ሰነድ ( የጽሁፍ፣ የቪዲዮ፣ የፎቶ) ፣ የሰው ማስረጃዎችን በዝርዝር መያዝ የሚገባው ሲሆን የሚቀርበው የሰው ማስረጃ በሆነ ጊዜ የምስክሮቹን ማንነት እና አድራሻ ዝርዝር አካቶ ሊይዝ ይገባል፥
  • ለቦርዱ ከመቅረቡ በፊት ጉዳዩ በሌሎች የምርጫ ማስፈፀሚያ አደረጃጀቶች ታይቶ ውሳኔ ተሰጥቶበት ከሆነ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ በሰጡ አካላት የተሰጡ ውሳኔዎች፣ የቀረቡ ማስረጃዎችና የማስረጃ ዝርዝር መግለጫዎች፣ ውሳኔ ካልተሰጠበትም ሁኔታው መጠቀስ ይኖርበታል
  • ከላይ በተገለፀው መሰረት አቤቱታ ለሚያቀርብ አቤቱታ አቅራቢ በአቤቱታው ቅጂ ላይ ቀንና ሰዓቱ ተመዝግቦ እና ተፈርሞ ማረጋገጫ ይሰጠዋል፡፡
  • ለአቤቱታው መልስ መስጠት ያለበት ሰው ካለ የዚሁ ሰው ስምና አድራሻ በአቤቱታው ላይ ሊመለከት ይገባል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ማስታወቂያ
ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም