ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ ከፍተኛ አቤቱታ የቀረበበት በሶማሌ ክልል እየተከናወነ ያለው የመራጮች ምዝገባ ሂደት ነው። በዚህ ሂደት ላይ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ለቦርዱ አቤቲታዎችን ያቀረቡ ሲሆን ( ኦብነግ፣ ነጻነት እና እኩልነት፣ ኢዜማ እና የግል እጩ ተወዳዳሪ)፣ ህጋዊ ያልሆነ የምዝገባ ሂደትን የሚያሳዩ ምስሎች እና ቪዲዎችም በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲታዩ ነበር፤ቦርዱም በሚዲያ ሞኒተሪንግ ክፍሉ ተሰበስቦ ቀርቦለት እነዚህን ምስሎች እና ቪዲዮዎች ተመልክቷል።

ከፓርቲዎች በተለያ ጊዜ በጋራ እና በተናጠል የቀረቡለት አቤቱታዎች ያተኮሩባቸውአንኩዋር ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፤

1. የመራጮች ምዝገባ ካርዶች የማይገባቸው ሰዎች እጅ ገብቷል፣ ከምርጫ ጣቢያ ውጪ ካርዶች ሲታደሉ ነበር።

2. ያልተሞሉ የመራጮች ምዝገባ ካርዶች ለዝቅተኛው መንግስት እርከን ( ቀበሌ ወረዳ ሰራተኞች) እና እጩዎች ተሰጥተዋል

3. የመራጮች ምዝገባ ሂደቱን የገዥው ፓርቲ የዝቅተኛ እርከን ሰራተኞች ከፍተኛ ጣልቃገብነት ነው የሚሰራው፣ በዚህም ምክንያት የመራጮች ምዝገባ በቦርዱ ቁጥጥር ስር አይደለም

4. የምርጫ አስፈጻሚዎች ከመንግስት አስተዳደር እርከን ሰራተኞች እና እጩዎች ጋር በዝምድና እና በተለያዩ መንገዶች የተያያዙ በመሆናቸው የገለልተኝነት ጥያቄ አለ

5. የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ዜጎች እንዳይመዘገቡ ክልከላ ተደርጎባቸዋል፣

6. የመራጮች ካርድ የወሰዱ ዜጎች እጅ ተመልሶ ተሰብስቧል

7. የመራጮች ካርድ ብሉ ቦክስ በምርጫ ጣቢያዎች ሲደርስ በተገቢው መንገድ ሳይታሸግ ነው ይህም በመካከል እንደተከፈተ ያሳያል… የሚሉ ናቸው። ለነዚህ አቤቱታዎች ዝርዝር የጽሁፍ አቤቱታ፣ የፎቶ፣ የቪዲዮ እና ሌሎች ማስረጃዎች ይሆናሉ የሚሉ ሰነዶችን አቅርበዋል።

አቤቲታዎቹን መሰረት በማድረግ ቦርዱ የሚከተሉትን ተግባራት አከናውኗል።

- አቤቱታ ካቀረቡ የፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር በማእከልም በክልሉም ውስጥ ውይይት አከናውኗል።

- በቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሚመራ አጣሪ ቡድን ወደ ክልሉ በመላክ ምርጫ ጣቢያዎችን፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን እና ሌሎች አካላትን አነጋግሯል።

- የቀረቡ አቤቱታዎችን እና ሰነዶችን በማየት ስብሰባ አከናውኖ የሚከተሉትን ዋና ዋና ውሳኔዎች ወስኗል።

የሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ ውሳኔ

1. የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ ላይ የቀረቡትን ዝርዝር አቤቱታዎች በስፋት መርምሯል፤ በማስረጃነት የቀረቡለትን ከ150 በላይ የሆኑ ባዶ እና ምዝገባ የተፈፀመባቸው የመራጭ ካርዶችን በመራጮች ምዝገባ ሲስተሙ ላይ ካለው ዳታ ጋር አገናዝቦ ተመልክቱዋል፤ የቀረቡ የቪዲዮ ማስረጃዎች (ትርጉም) እና ምስሎችን ከአቤቱታው ጋር አገናዝቧል።

በእነዚህ ሂደቶች ከተመለከታቸው ዝንባሌዎች (trends) በአቤት ባዮቹ የተጠቀሱት ብልሹ አሰራሮች ተፈፅመው ሊሆን እንደሚችል ግንዛቤ በመውሰድ፤ይህ ሁኔታም በሂደቱ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ የሚፈጥር መሆኑን እነዲሁም መጣራትን ለመጀመር በቂ የሆነ መረጃ እንዳለ በመገንዘብ ከፍተኛ የሆነ የመራጮች ምዝገባ ሂደት የአሰራር መዛባት አቤቱታ የቀረበባቸው በሶማሌ ክልል የሚገኙ የሚከተሉት የምርጫ ክልሎች ላይ የመራጮች ምዝገባ በጊዜያዊነት አንዲቆም ወስኗል። እነዚህም

- የምርጫ ክልል አራቢ ( ለክልል ምክር ቤት አውበሬ እና ደንበል ከተማ ምርጫ ክልሎችን የሚያካትት)

- ምርጫ ክልል ደግሃመዶ

- የምርጫ ክልል ጎዴ ( ለክልል ምክር ቤት አዳድሌ፣ ቤርአኖ፣ ደናን፣ ምስራቅ ኢሚ፣ ኤልወይኔ፣ ጎዴ፣ ጎዴ ከተማ የምርጫ ክልሎችን የሚያካትት)

- የምርጫ ክልል ጂጂጋ 1 ( ለክልል ምክር ቤት ጂግጂጋ፣ ጂግጂጋ ከተማ፣ ቱሉ ጉድሌ ምርጫ ክልሎችን የሚያካትት)

- ምርጫ ክልል ቀብሪደሃር ( ለክልል ምክር ቤት ደበወይን፣ ቀብሪደሃር፣ ቀብሪደሃር ከተማ፣ መርሲን፣ ሼኮሽ እና ሺላሎ ምርጫ ክልሎችን የሚያካትት)

- ምርጫ ክልል ቀላፎ ( ለክልል ምክር ቤት ፊርፊር እና ቀለፎ የምርጫ ክልሎችን የሚያካትት)

- ምርጫ ክልል ዋርዴር ( ለክልል ምክር ቤት ደራቴሌ እና ዋርዴር ምርጫ ክልሎችን የሚያካትት)

2. ከላይ በተጠቀሱት የምርጫ ክልሎች ላይ ያለው የመራጮች ምዝገባ ሂደት በጊዜያዊነት ሲቆም አስፈጻሚዎች እና የሚመለከታቸው የቦርዱ ኦፕሬሽን ሰራተኞች የሚወስዱትን እርምጃ አስመልክቶ መመሪያ የተዘጋጀ ሲሆን በዚያ መመሪያ መሰረት ተፈጻሚ ይሆናል።

3. ከላይ በተጠቀሱት የምርጫ ክልሎች ላይ ያለውን የመራጮች ምዝገባ ሂደት የሚያጣራ ቡድን ቦርዱ የሚያቋቁም ሲሆን በዚህም የማጣራት ሂደት ውስጥ የአቤቱታ አቅራቢ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ የቦርዱ ሰራተኞች እና ገለልተኛ ባለሞያዎች የማጣራት ሂደቱን እንዴት ሊያከናውኑት እንደሚገባ የሚመራ የቴክኒክ ዝርዝር መመሪያን አዘጋጅቶ ወደተግባር የሚገባ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ሚያዝያ 30 ቀን 2013 ዓ.ም