ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫን ተግባራት እያከናውነ ቆይቶ የመራጮች ምዝገባ መጠናቀቁ እና የመራጮች ምዝገብ ይፋ መደረጉ ይታወቃል። የመራጮች ምዝገባ ሂደት ከሞላ ጎደል በስኬታማነት የተጠናቀቀ ቢሆንም ሂደቱ እየተከናወነበት ባለበት ጊዜ አንስቶ የሚታዪ በተለይ የዝቅተኛ የመንግስት እርከን ሰራተኞች(ወረዳ፣ ቀበሌ…ወዘተ) ጣልቃ ገብነቶችን በተለያየ መንገድ ለሚመለከታቸው አካላት ሲያሳውቅ ቆይቷል። በቅርቡም ቦርዱ በግንባር ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመሄድ በነጻ የስልክ ጥሪ መስመር የሚመጡ ጥቆማዎችን በመከታተል፣ የክትትል ቡድኑን በማሰማራት የምዝገባ ሂደቱን ለመገምገም ሞክሯል።
በዚህም መሰረት የዝቅተኛ የመንግስት እርከን ላይ የሚገኙ ሰራተኞች ምርጫ ጣቢያ ላይ ያለምንም ከቦርዱ የሚሰጥ የፓርቲ ወኪልነትን የሚያሳይ መታወቂያ መገኘት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን መረጃ መጠየቅ እና በአንዳንድ ሁኔታዎች የመራጮች ምዝገብን ለመጎብኘት እና መረጃዎችን ለመውሰድ ጥረት በማድረግ ጣልቃ መግባታቸውን ተረድቷል። ይህ በተለይ ወደ ድምጽ መስጫ ቀን እየተጠጋን በመጣን ጊዜ የምርጫ ሂደቱን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያውከው ከመሆኑም በላይ በምርጫ ህጉም ሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ የተቀመጠ ወንጀል በመሆኑ
- ማንኛውም የዝቅተኛው መንግስት እርከን ሰራተኛ (ቀበሌ፣ ወረዳ….) ወይም ያልተፈቀደለት ሌላ አካል ምርጫ ጣቢያ ውስጥም ሆነ 200 ሜትር ርቀት ዙሪያ ላይ እንዳይገኝ
- ቦርዱ ለፓርቲ ወኪሎች የእውቅና ባጅ በመስጠቱ የእውቅና ባጅ ከተሰጣቸው ፓርቲ ወኪሎች ውጪ ማንኛውም አካል የመራጮች ምዝገብ እና ተመዝጋቢዎች መረጃን አስመልክቶ ምርጫ ጣቢያም ሆነ የምርጫ ክልል አስፈጻሚዎችን እንዳይጠይቅ እንዲሁም በምርጫ ጣቢያው ውስጥ እና በ200 ሜትር ርቀት ዙሪያ እንዳይገኝ
- ማንኛውም የመንግስት እርከን ሰራተኛ ከቦርዱ የበላይ ሃላፊዎች እውቅና በማግኘት ወይም በልዩ የደህንነት ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር ለምርጫ አስፈጻሚች ከምርጫ ጋር የተገናኘ ቁሳቁሶችን እንዲያቀንቀሳቅሱ፣ ትእዛዝ አቅጣጫ እና ጥቆማ እንዳይሰጥ እጅግ በጥብቅ ያሳስበባል።
ይህ ሆኖ ቢገኝ ግን የምርጫ ወንጀል በመሆኑ ይህንን ተግባር የፈጸሙ ግለሰቦች በምርጫ ህጉ እና በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ተጠያቂ እንደሚሆኑ እየገለጽን የቦርዱ ምርጫ አስፈጻሚዎችም ማንኛውም የዝቅተኛ የመንግስት እርከን ሰራተኞች ወይም ሌሎች ያልተፈቀደላቸው አካላት ከምርጫ ጣቢያ ውስጥም ሆነ 200 ሜትር ርቀት ውስጥ እንዳይገኙ እንዲያደርጉ፣ ከቦርዱ ሰራተኞች እና ሃላፊዎች ውጪ ምንም አይነት ትእዛዝም ሆነ አቅጣጫ በፍጹም እንዳይቀበሉ በዚሁ አጋጣሚ እናሳስባለን።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ግንቦት 16 ቀን 2013 ዓ.ም