Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዕጩዎች የምዝገባ ሂደትንና አጠቃላይ የኦፕሬሽን ሂደቶችን የተመለከተ የምክክር መድረክ አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 8 ቀን 2013 ዓ.ም. የዕጩዎች የምዝገባና አጠቃላይ የኦፕሬሽን ሂደቶችን የተመለከተ የምክክር መድረክ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የብዙኃን መገናኛ አካላት በተገኙበት አካሄደ። ይህን የምርጫው የጊዜ ሠሌዳ ከወጣበት ጊዜ አንሥቶ በተከታታይና በልዩ ሁኔታ እየተደረጉ ያሉ የምክክር መድረኮች አካል የሆነውን መርኃ-ግብር በንግግር ያስጀመሩት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ሲሆኑ፤ የዕጩዎች ምዝገባና ተያያዥ የኦፕሬሽን ሥራዎችን የተመለከቱ አጠቃላይ ገለጻ ሰጥተዋል። ግልጽነትና ፍትሐዊነትን ለመጨመር ያስችል ዘንድ በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የሚኖረውን የዕጩዎች ቅደም ተከተል በሎተሪ ዕጣ እንደሚወሠንም አክለው ገልጸዋል። የሰብሳቢዋን ማብራሪያ ተከትሎ የቦርዱ የኦፕሬሽን ክፍል ባልደረባ በዕጩዎች ምዝገባ ወቅት የቀረቡ አቤቱታዎችንና መልስ የተሰጠበትን አግባብ አብራርተው የተሣታፊዎች ሃሳብ አሰተያየት እንዲሰጡበት ተደርጓል።

ሀሳባቸውን ከሰጡ ተሣታፊዎች ውስጥ በዕጩዎች ምዝገባ ሂደት በእሥር ላይ በመሆናቸው መመዝገብ ሳይችሉ ቀርተው በቦርዱ ጥረት ተፈትተው የተመዘገቡ ዕጩ አንዱ ሲሆኑ፤ ቦርዱን ተከታትሎ ስላስፈታቸውና በዕጩነት እንዲመዘገቡ ስላስቻላቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል። እኚሁ ዕጩ በአካባቢያቸው ላይ አሉ ያሉትን ሥጋቶች ገልጸው ቦርዱ እልባት እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል። በተመሳሳይ መልኩ ሌሎችም ፖለቲካ ፓርቲዎች በዕጩዎች ምዝገባ ወቅት ያጓጠሟቸውን ዕክሎች በመግለጽ፤ አቤቱታ ካቀረቡ በኋላ ላገኙት ፈጣን ምላሽ ቦርዱን አመስግነዋል። ፓርቲዎቹ አልተፈቱልንም ያሏቸውን ችግሮችም እንዲሁ አስረድተዋል።

በዕጩዎች ምዝገባ ወቅት ለሚኖሩ አቤቱታዎች በአጭር ጽሑፍ መልዕክትና በስልክ እንዲሁም ፓርቲዎቹ ይቀሉናል ባሏቸው አማራጮች ሁሉ በመጠቀም መፍትሔ እንዲያገኙ እንደመመቻቸቱ መጠን፤ የዕጩዎች ምዝገባ መጠናቀቁን ተከትሎ የሚቀርቡትን አቤቱታዎች ለማስተናገድ ቦርዱ እንደሚቸግር ተገልጿል። ያም ሆኖ ግን በበቂ መረጃ ተደግፈው በክትትል ላይ ያሉ ጉዳዮችን እንደሚመልስና የዕጩዎች ምዝገባም ፍጽም ዝግ ነው ማለት እንዳልሆነ ተብራርቷል።

የምርጫ ክርክር ሂደት ምክር‘ሃሳብ ሌላኛው የምክክር መድረኩ አጀንዳ የነበረ ሲሆን፤ በቦርዱ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ አማካኝነት ቀርቧል። አማካሪዋ ቦርዱ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ከብዙኃን መገናኛዎች የምርጫ ክርክር ለማካሄድ አስበው የክርክሩን ሥርዓት የሚያስተናግዱበትን አግባብ በተመለከተ ከቦርዱ እገዛ በጠየቁት መሠረት ቦርዱ የፍላጎት ማቅረቢያ ቅጽ ማዘጋጀቱን እና ለሁሉም ክፍት የሆነ ጥሪ ማካሄዱን አብራርተዋል። በዚህም መሠረት 23 ድርጅቶች ማመልከቻ ያስገቡ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ አምስቱ ብዙኃን መገናኛ እንደሆኑ ተገልጿል። የፍላጎት ማቅረቢያ ምዝናው እንዴት እንደሆነና የቀረቡት ማመልከቻዎች ይዘትና ውሥንነትም አብሮ ተብራርቷል።

ተሣታፊዎቹ በቀረበው ሃሳብ ላይ አስተያየት የሰጡበት ሲሆን በቦርዱ ዋና ሰብሳቢና በኮሚኒኬሽን ሃላፊዋ አማካኝነት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። ዋና ሰብሳቢዋ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና በብዙኃን መገናኛዎች የቀረቡትን ማመልከቻዎች ዝርዝር ይዘት ማወቅ የፈለገ ፓርቲ ከቦርዱ የኮሚኒኬሽን ክፍል መጥቶ መውሰድ እንደሚችል የገለጹ ሲሆን፤ ማመልከቻ መውሰጃ ጊዜው እስከ ሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀነ-ገደበ ተቀምጦለታል።

Share this post