Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫን ደኅንነት አጠባበቅ አስመልክቶ ለከፍተኛ ፖሊስ መኮንኖች ሥልጠና ሰጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከመጋቢት 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናቶች የምርጫን ደኅንነት አጠባበቅ አስመልክቶ ለከፍተኛ ፖሊስ መኮንኖች የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጠ፡፡ ይህን ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የሚሰጥ የአሠልጣኞች ሥልጠና በንግግር ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ ሲሆኑ፤ ለምርጫው ስኬታማነት የምርጫው ፀጥታና ሰላም ወሣኝነትን ገልጸው፤ ሠልጣኞቹ የሥልጠናውን የድርጊት መርኅ-ግብር ምንም ሳይጓደል በየደረጃው ላሉ የፀጥታ አስከባሪ አካላት እንዲያወርዱት ጠይቀው፤ ለተሣታፊዎቹና ለአስተባባሪዎቹ በሙሉ ያላቸውን ምስጋና ገልጸዋል። የቦርዱን ምክትል ሰብሳቢ ንግግር ተከትሎ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ ባረደጉት ንግግር፤ ከሕዝብ የተቀበልነውን አደራ ገለልትኛ በሆነ መልኩ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ሳንቆጥብ ሕዝብ ሊረካበትና ሊደሰትበት የሚችል ሥራ ሕግና ሕግን ብቻ ተከትለን ልንሠራ ይገባል ያሉ ሲሆን፤ ሠልጣኞችም የሥልጠናውን ዝርዝር ግኝቶች ምንም ሳይጓደሉ ወደታች በሚደርስበት አግባብ ሥልጠናውን እንዲወስዱ አሳስበዋል።

ሥልጠናው ከፌደራልና ከዘጠኙ ክልሎች እንዲሁም ከሁለቱ ከተማ መስተዳደሮች ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጡ ተወካዮች የሚሣተፉበት ነው። የምርጫ አፈጻጸም የሕግ ማዕቀፍ፣ የምርጫ ቅስቀሳ ሕጋዊ መብቶችና ገደቦች፣ የምርጫ ጣቢያ ሥርዓት ሂደት፣ የግጭት አፈታት ሥርዓት፣ ለኮቪድ 19 መከላከል ሊወሰዱ የሚገቡ ዕርምጃዎች፣ በምርጫ ሂደት ላይ ሰላምና ፀጥታን የሚያስከብሩ የፀጥታ አስከባሪ አካላት የአሠራር ሥርዓት እና የሥነ-ምግባር መመሪያን የተመለከቱ ዝርዝር ድንጋጌዎች በሥልጠናው ውስጥ ከተካተቱ አጀንዳዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ይህ ለሦስት ቀን የቆየው ሥልጠና በቅድመ ሥልጠና የሙከራ ፈተና የተጀመረ ሲሆን፤ ሠልጣኞቹ ከሥልጠናው በኋላ በየደረጃው ላሉ የፀጥታ አስከባሪዎች ሥልጠና እንዲሰጡ ይደረጋል።

Share this post