Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛውን አጠቃላይ ምርጫ ለመታዘብ ፈቃድ ለተሰጣቸው ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. 6ኛውን አጠቃላይ ምርጫ ለመታዘብ ፈቃድ ለተሰጣቸው ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሄደ። መርኃ-ግብሩን የቦርዱ አመራር የሆኑት ፍቅሬ ገ/ሕይወት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የተከፈተ ሲሆን፤ የቦርዱ የሥራ ክፍሎች እንደየሥራ ክፍላቸው የምርጫውን ሂደት የተመለከተ አጠቃላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የቦርዱን አደረጃጀትና በየደረጃው ያሉ ቢሮዎች ኃላፊነት፣ በቦርዱ የተሰጡ ሥልጠናዎች፣ የዕጩዎች ምዝገባ፣ የሠነዶች እና ቁሳቁሶች ዝግጅትና ሥርጭት፣ የመራጮች ምዝገባ ቅጾችና ዝግጅት እንዲሁም ተያያዥ አጠቃላይ የኦፕሬሽን ሥራዎችን የተመለከቱ ማብራሪያዎች በቦርዱ የኦፕሬሽን ክፍል ባልደረባ ሲቀርብ፤ በምርጫ ወቅት የኮቪድ 19 ሥርጭትን ለመቀነስ የወጣ መመሪያን አስመልክቶ በቦርዱ የኮቪድ አስተባባሪ አማካኝንት ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፤ የመራጮች ምዝገባና አካታችነት ከሥርዓተ-ፆታ፣ ከአካል ጉዳተኞች እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን አስመልክቶ በቦርዱ የሥርዓተ-ፆታ እና አካታችነት ኃላፊ አማካኝነት እንዲሁም የመራጮች ምዝገባ እና የሀገር ውስጥ ምርጫ ታዛቢዎች ፈቃድ አሰጣጥ፣ አሠራር እና ሥነ-ምግባር መመሪያን የተመለከተ ማብራሪያ ደግሞ በቦርዱ የሕግ ክፍል ባልደረባ አማካኝነት ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

ከላይ ከተጠቀሱት ማራሪያዎች በተጨማሪ የምርጫ መታዘብ ክትትል እና ድጋፍ ረቂቅ ማዕቀፍ አስመልክቶ በሀገር ውስጥና ዓለም ዐቀፍ የምርጫ ታዛቢ ባለሙያ አማካኝነት እንዲሁም ከምርጫ ሂደት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ግጭቶች ሪፖርት አደራረግን አስመልክቶ ደግሞ የምርጫ ወቅት ግጭት መከላከል ባለሞያ አማካኝነት ቀርቧል። ማብራሪያዎቹን ተከትሎ ከተሣታፊዎቹ በርካታ ጥየቄዎች የተነሡ ሲሆን ሁሉም መልስ ተሰጥቶባቸዋል። ለተሣታፊ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ የቦርዱ አመራር በሆኑት ፍቅሬ ገ/ሕይወት አማካኝነት የፈቃድ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸው መርኃ-ግብሩ ተጠናቋል። አቶ ፍቅሬ በመርኃ-ግብሩ ላይ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ተቋማቱ በምርጫው ሂደት ላይ በሚኖራቸው ተሣትፎ በዐዋጁና በመመሪያዎቹ ላይ የተቀመጡትን ደንቦቸ በተከተለ መንገድ እንዲሆን አሳስበዋል።

 

Share this post