Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመረጮች ምዝገባና አጠቃላይ የኦፕሬሽን ሂደቶችን ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን አስመልክቶ ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች ሪፓርት አቀረበ

መድረኩን የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የመሩት ሲሆን፤ ምርጫ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን የሚያሣትፍ መድረክ እንደሆነና ከባለድርሻ አካላቱ መካከልም ፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ እንደመሆናቸው መጠን ስሕተቱንም ስኬቱንም እንዲያውቁ በማድረግ እየተራረሙ ለመሄድ በተከታታይ እየተዘጋጁ ያሉት መድረኮችን ማዘጋጀት እንዳስፈለገ ገልጸዋል። የሰብሳቢዋን ንግግር ተከትሎ የቦርዱ የኦፕሬሽን ክፍል ባልደረቦች ለምርጫ ምዝገባ የሚውሉ ቁሳቁሶች የግዢ አፈጻጸም፤ ሥርጭትና የሰው ኃይል ሥምሪትን፣ የቁሳቁሶች ጥራትና ደኅንነት አጠባበቅን፣ እንዲሁም ከምርጫ ጣቢያዎች አከፋፈት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።

የመድረኩ ተሣታፊዎች ማብራሪያውን ተከትሎ አስተያየታቸውን ያጋሩ ሲሆን፤ ምንም እንኳን በቦርዱ ጥረትና ግልጽ አሠራር ደስተኛ እንደሆኑ ቢገልጹም፤ በብዙኃን መገናኛ ነፃ የዐየር ሰዓት አጠቃቀም ዙሪያ፣ በዐደባባይ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች፣ በእጩዎች ላይ እየደረሱ ያሉ ማስፈራሪያዎችንና እስሮች እንዲሁም የምርጫ ጣቢያዎች በሚፈለገው ቁጥር ልክ ያለመከፈትና ከሚጠበቀው አንጻር አናሳ ሆኖ ተገኝቷል ባሉት የተመዘገቡ የመራጮች ቁጥር ዙሪያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ከተሣታፊዎቹ ለቀረቡት አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ዋና ሰብሳቢዋ በሰጡት ምላሽ፣ የመራጮች ምዝገባ በተፈለገው መልኩ እየሄደ ነው ማለት እንደማይቻል ገልጸው፣ ጉዳዩ በመራጮች ማስተማር ዙሪያ የተሠማሩ የሲቪል ማኅበራትና ፖለቲካ ፓርቲዎችም እገዛ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል። ከቁሳቁስ ሥርጭት አንጻር የሎጄስቲክስ ችግሮች እና አቅም፣ የአካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታና የጂኦግራፊ አቀማመጥ ተግዳሮቶች እንደነበሩ የገለጹ ሲሆን እስካሁን የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው አፋር እና ሶማሌ ክልሎች እንዳሉ፤ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ባቀረቡት እሥርና ተያያዝ አቤቱታዎች ጋር በተገናኘ ፓርቲዎቹ በጥቅል እንዲህ ገጠመን ማለት ብቻ ሣይሆን በበቂ በማስረጃ አስደግፈው ቢያቀርቡ ተባብሮ መፍትሔ ለማሰጠት እንደሚረዳ ገልጸዋል።

ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ገዢው ፓርቲ ላይ ለቀረቡት አቤቱታዎች የገዢው ፓርቲ ተወካይ አቶ ብናልፍ አንዱአለም መልስ የሰጡ ሲሆን፤ ደረሱ በተባሉት እስሮች በጣም እንደሚያዝኑና ከዚህ በኋላ መሠል ነገሮች እንደማይፈጠሩ ቃል በመግባት ጭምር ተናግረዋል። ተወካዩ አያይዘውም ፓርቲዎቹ በወቀሳ አቀራረብ ወቅት ምንም እንዳልተሠራ ተደርጎ የሚገለጽበትን አግባብ ወቅሰው፤ ኃላፊነት መወጣቱ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ተደርጉ የሚወሰድበት አግባብ ልክ እንዳልሆነ አሳስበዋል። በመንግስት በኩልም ቦርዱን ለማገዝ የሚያስፈልጉ ትብብሮች እንደሚደረጉ ገልጸዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ በሚቀጥለው ተከታይ ውይይት የመራጮች ምዝገባ ቀናትን እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ውይይት እንደሚኖር የተገለጸ ሲሆን በአጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎችን መክፈት እና ምዝገባን አስመልክቶ የሚቀጥሉት 7 ቀናት የሚኖረውን ሁኔታ ቦርዱ በተጨማሪ እንደሚያሳወቅ ተገልጿል።

Share this post