Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለመራጮች ት/ት ፍቃድ ከተሰጣቸው የሲቪክ ማኅበራት ድርጀቶች ጋር ውይይት አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅዳሜ የካቲት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ለመራጮች ት/ት ፍቃድ ከተሰጣቸው የሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች ጋር የጀመረውን ውይይት በትላንትናው ዕለት የካቲት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. አጠናቋል። የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የተጀመረው የውይይት መድረክ የተለያዩ ክፍሎች የነበሩት ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ የተለያዩ ሀገራት ልምዶች ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮ ባላቸው ባለሞያ ሲቀርብ፤ የመራጮች ት/ት ፍቃድ አሰጣጥ እና የሥነ-ምግባር መመሪያ ቁጥር 4/2012 ላይ የሠፈሩትን መሠረታዊ ደንቦች ከሲቪክ ማኅበራት ኃላፊነት አንጻር በቦርዱ አመራር አባል አበራ ደገፋ (ዶ/ር) ቀርቧል። ለሲቪክ ማኅበራት የተዘጋጀ ማስታወሻ፣ የማስተማሪያ መንገድ እና ማንዋል መመዘኛ ቅጽ፣ የሥነ-ምግባር ደንብ እንዲሁም በመራጮች ት/ት ጊዜ መነሣት/መካተት ያለባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች በቦርዱ የሲቪክና የመራጮች ትምህርት ክፍል ባልደረቦች አማካኝነት ተብራርቷል። በቀረቡት ገለጻዎች ላይ ተሣታፊዎች አስተያየት እንዲሰጡበት የተደረገ ሲሆን፤ መልስ የሚሹትን አስተያየቶች በቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለና በቦርዱ አመራር አባል አበራ ደገፋ (ዶ/ር) አማካኝነት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

የመራጮች ት/ት አሰጣጥ ላይ የኮቪድ 19 መመሪያ እና የሥነ-ምግባር ድንብን ማስተዋወቅ ሌላው የውይይቱ አጀንዳ የነበረ ሲሆን በቦርዱ የኮቪድ 19 አስተባባሪ አማካኝነት ገለጻ ተሰጥቶበት ውይይት ተካሂዶበታል። አካታች የሆነ የመራጮች ት/ት አስፈላጊነት፤ ከሥልጠናው የሚጠበቁ ወጤቶች እና ምርጫውን አካታች ለማድረግ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች የቀረቡ ሲሆን፤ የሥርዓተ-ፆታና የአካል ጉዳተኞች አካታችነት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኃላፊነት መሆኑ ከፍተኛ አጽንኦት ተሰጥቶበታል። በፕሮግራሙ ማብቂያ ላይ የቦርዱ አመራር አባል አበራ ደገፋ (ዶ/ር) ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ በንግግራቸውም ት/ት አሰጣጡ የሥነ-ምግባር ደንቡንና የማሠልጠኛ ማንዋሉን በተከተለ መንገድ እንዲሆን እንዲሁም ገለልተኝነትን ማንጸባረቅ እንደሚያስፈልግና የተደራሹን ማኅበረሰብ ልዩ ባሕሪያት፣ ዕድሜና የትምህርት ደረጃ እንዲሁም ትምህርት የሚሰጥበትን የጊዜ ሠሌዳ ባገናዘበ መልኩ ሊሆን እንድሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

 

Share this post