የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖሊቲካ ፓርቲዎች እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና ቦርዱን ባቋቋመው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 133/2011 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ ምርጫውን ለመዘገብ ለሚፈልጉ የመገናኛ ብዙሃን እና ጋዜጠኞች ፈቃድ ለመስጠት እና ለመከታተል የሚያስችለውን መመሪያ አርቅቆ፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የስነ ምግባር እና አሰራር መመሪያ ቁጥር 02 /2013 አፅድቋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ቀጣዩ 6ተኛ አጠቃላይ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ሚዛናዊ እና ትክክለኛ እንዲሆን የሚያበረክቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ፤የመገናኛ ብዙሃን እና ጋዜጠኞች በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው ለመዘገብ የሚያስችል የፍቃድ ጥያቄያቸውን ለቦርዱ እንዲያቀርቡ ይህንን ጥሪ ማድረግ አስፈልጓል፡፡ በዚህ መሠረት ለመዘገብ ጥያቄ የሚያቀርቡ የመገናኛ ብዙሀን

• ቦርዱ ያዘጋጀውን የማመልከቻ ፎርም

• የጋዜጠኞች ዝርዝር የሚገልጽ ፎርም

• የሚዲያ ተቋሙ የሚያሰማራቸው ጋዜጠኞች የገለልተኝነት ማረጋገጫ ቃለመሃላን ጀምሮ የተለያዩ አስፈላጊ ተያያዥ ሰነዶችን በማቅረብ የዘገባ እውቅና እንዲሰጣቸው ማቅረብ ይችላሉ።

መገናኛ ብዙሃን የማመልከቻ ቅጹን እና አስፈላጊ ሰነዶችን ከቦርዱ ድረ-ገጽ ወይም ከቦርዱ ዋና መስሪያ ቤት እና የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መውሰድ የምትችሉ ሲሆን የተጠናቀቁ ማመልከቻዎቻችሁን በኢሜል አድራሻችን media [at] nebe.org.et መላክ ወይም ለዋናው መስሪያ ቤት እና ለክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ይህ ማስታወቂያ ከወጣበት ከየካቲት 01 ቀን ጀምሮ ለ10 ተከታታይ የስራ ቀናት ማስገባት ትችላላችሁ።

ማስታወሻ

ይህ የመጀመሪያ ዙር እውቅና አሰጣጥ ሲሆን በየደረጃው የተለያዩ ዙሮች እውቅና መስጠቱ ሂደት የሚቀጥል ይሆናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የጥሪ ማስታወቂያ
የካቲት 01 ቀን 2013 ዓ.ም