የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን የአሠልጣኞች ሥልጠና ዛሬ ጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም አጠናቋል። ለምርጫ ክልል ኃላፊዎች፣ ለምርጫ ጣቢያ ሠራተኞችና በተለያየ ደረጃ ላሉ የIT ባለሞያዎች ለመስጠት የታቀደው ሥልጠና አካል የሆነውን ይህን የአሠልጣኞች ሥልጠና በንግግር የከፈቱት የቦርዱ አመራር የሆኑት ፍቅሬ ገብረሕይወት ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም የሥልጠናውን አስፈላጊነት እንዲሁን ከኮቪድ አንጻር ሊወሰዱ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች አጽንኦት ሰጥተውበታል።
የምርጫ የሕግ-ማዕቀፎች፣ የምርጫ ክልል ቢሮዎች ግዴታና ኃላፊነቶች፣ ለኮቪድ መከላከል ሊወሰዱ የሚገቡ ዕርምጃዎች፣ የምርጫ ቅሬታ አፈታቶች፣ የምርጫ ነክ ሎጀስቲክና ፀጥታ ሁኔታዎች፣ የሥርዓተ-ፆታና አካል ጉዳተኛ አካታችነት፣ የዕጩዎች ምዝገባ ሂደት፣ ለዕጩዎች ምዝገባ ሂደት የሚውሉ ሶፍትዌሮችና አተገባበራቸው እንዲሁም ሊፈጠሩ የሚችሉ ተገማች ቴክኒካል ዕክሎችና አፈታታቸው ሥልጠናው ውስጥ ከተካተቱት አጀንዳዎች ውስጥ ይገኙበታል። ይህ ስልጠና በቀጣይ ክፍሉ ለመሪ አሰልጣኞች (Lead trainers) የሚሰጥ ሲሆን እነዚህ መሪ አሰልጣኞች ደግሞ ወደተለያዩ ክልሎች በመሰማራት ምርጫ አስፈጻሚዎችን የሚያሰለጥኑ ይሆናል።