የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው አገራዊ ምርጫ ዝግጅት ከሚያደርጋቸው ዝግጅቶች አንዱ በየደረጃው ምርጫ የሚያስፈጽሙ አስፈጻሚዎችን መልምሎ በማሰልጠን ለስራ ማሰማራት ነው። ከዚህ በፊት በተለያዩ ምክክሮች ከፓርቲዎች በተደጋጋሚ እንደተነሳው እንዲሁም የሂደቱን ተአማኒነት እና ገለልተኝነት ለማረጋገጥ ምርጫ ቦርድ ካለው ቁርጠኝነት በመነሳት ለመጀመሪያ ዙር የተመለመሉ የምርጫ ክልል ደረጃ ምርጫ አስፈጻሚዎችን ዝርዝር ለፖለቲካ ፓርቲዎች ለማጋራት ዝግጁ አድርጓል። በዚህም መሰረት ፓርቲዎች በቦርዱ ዋና መስሪያ ቤት በመገኘት በሶፍት ኮፒ (ለእያንዳንዱ ፓርቲ በፍላሽ) የተዘጋጀውን የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያቸው የተጠናቀቁ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ዝርዝር እንዲወስዱ እና ገለልተኝነታቸው ላይ አስተያቶች ካሏቸው እንዲያሳውቁ ጥሪውን ቀርባል። በተጨማሪም በቀጣይ ዙሮች የምርጫ አስፈጻሚዎችን ዝርዝር ቦርዱ የሚያጋራ ሲሆን ፓርቲዎችም በተመሳሳይ የሚደርሷቸውን አስፈጻሚዎች ዝርዝር ከገለልተኝነት አንጻር በመፈተሽ ለቀጣዩ ምርጫ ተአማኒነት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪውን ያቀርባል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
የጥሪ ማስታወቂያ
ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም