የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በህግ ከተቋቋመባቸው ዋና ዋና ተግባራት አንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ፥ ቁጥጥር እና ክትትል ነው። በመሆኑም በምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት ፓርቲዎች የተለያዩ መስፈርቶችን ማሟላታቸውን ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም መሰረት ቀደም ብሎ መስፈርት አሟልተው ምዝገባቸው የተጠናቀቀ እና በሂደት ላይ ያሉ ፓርቲዎች ዝርዝርን ማሳወቁ ይታወሳል። ቦርዱ ከዚህ ቀደም ውሳኔ ያልሰጠባቸው እንዲሁም የተጠየቁትን ማብራሪያዎች ያቀረቡ ፓርቲዎችን አስመልክቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል።
1. ቦርዱ ህዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ሕወሃት) የአመጻ ተግባር ላይ ተሰማርቷል ወይ የሚለውን ሁኔታ ለማጣራት በፓርቲው የተሰጡ መግለጫዎችን እና በይፋ የሚታወቁ ጥሬ ሃቆችን በማቅረብ ፓርቲው ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጻ ተግባር ላይ መሣተፉን አረጋግጧል፡፡ በተጨማሪም ፓርቲው መልስ የመስጠት እድል እንዲኖረው በማሰብ በፓርቲው እና በቦርዱ መካከል አገናኝ በመሆን ይሰሩ የነበሩትን የፓርቲውን የአዲስ አበባ ቢሮ የቀድሞ ተወካይ ለማነጋገር ጥረት ያደረገ ሲሆን ተወካዮም ፓርቲውን መወከል እንደማይችሉ ገልጸዋል። በመሆኑም፦
ሀ. በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 98/1//4/ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ህጋዊ ሰውነት ሰርዞታል። በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 99 መሠረት የፓርቲው ኃላፊዎች በፓርቲው ስም መንቀሳቀስ እንደማይችሉም ውሳኔ አስተላልፏል።
ለ. የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በፓርቲው እና በፓርቲው አመራሮች ላይ በሚያደርገው ምርመራ የሚገኙ በህወሐት ሥም የተመዘገቡ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ንብረቶችን በተመለከተ ያገኘውን ዝርዝር መረጃ እንዲልክ ቦርዱ ጥያቄ አቅርቧል።
ሐ. የፓርቲው ንብረት በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 99/2/ መሠረት ንብረቱ ተጣርቶ ዕዳ ካለበት ለዕዳው መሸፈኛ እንዲውል፤ ይሁንና እዳውን ሸፍኖ የሚተርፍ ንብረት ከተገኘ ቀሪው ገንዘብና ንብረት በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 99/3/ መሠረት ለሥነ ዜጋና መራጮች ትምህርት እንዲውል ቦር ወስኗል፡፡
2. ቦርዱ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሶስት ፓርቲዎችን ላይ በቦርዱ የትግራይ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በቀረቡ መረጃዎች እና ሌሎች ጥቆማዎች መሰረት ተጨማሪ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ስለእንቅስቃሴያቸው ማብራሪያ እንዲያቀርቡ ትእዛዝ ሰጥቷል። ትእዛዝ የተሰጣቸው ፓርቲዎችም የሚከተሉት ናቸው።
ሀ. “ዓሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ /ዓዴፓ/”- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምዝገባ ሂደት ላይ እያሉ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በተካሄደ ህገወጥ ምርጫ ስለመሳተፋቸው
ለ. “ብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ /ባይቶና/” - በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምዝገባ ሂደት ላይ እያሉ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በተካሄደ ህገወጥ ምርጫ ስለመሳተፋቸው እንዲሁም የፓርቲው አመራሮች በአመጻ ተግባር በመሳተፋቸው ለቦርዱ መረጃ በመድረሱ
ሐ. “ሳልሳይ ወያነ ትግራይ /ሣወት/”- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምዝገባ ሂደት ላይ እያሉ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በተካሄደ ህገወጥ ምርጫ ስለመሳተፋቸው እንዲሁም የፓርቲው አመራሮች በአመጻ ተግባር በመሳተፋቸው በቦርዱ መረጃ በመድረሱ
3. የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የመሥራች አባላት ጉዳይን አስመልክቶ ፓርቲው ያቀረበው የመሥራች አባላት ዝርዝር ላይ ቦርዱ 50 የሚሆን ናሙና በመውሰድ ያደረገው ማጣራት ስለ ትክክለኛነቱ ከፍተኛ ጥርጣሬ ውስጥ ያስገባው በመሆኑ፤ ቦርዱ ጉዳዩን ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ልኮት እንደነበር ይታወሳል። የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንም ባደረገው የማጣራት ሥራ ከሶማሌ ክልል 1145 መሥራች አባላት፣ ከአፋር ክልል 72 መሥራች አባላት፣ ከኦሮሚያ ክልል 23 መሥራች አባላት፣ ከአ.አ. ከተማ አስተዳደር 58 መሥራች አባላት በጠቅላላው የ1298 መሥራች አባላት በተጠቀሱት አድራሻ ያለመኖራቸውን ማረጋገጡን የሚያስረዳ መግለጫ በመስጠቱ የቦርዱም ሆነ የፖሊስ ኮሚሽኑ የማጣራት ሥራ የሚያሣየው ፓርቲው እያወቀ ወይም ማወቅ እየተገባው በቃለመኃላ በተረጋገጠ ሰነድ ያቀረበው የመሥራች አባላት ሥም ዝርዝር በተጭበረበረ ተግባር የፓርቲውን የዳግም ምዝገባውን ሂደት ማስፈጸም መፈለጉን እንደሆነ ተረድቷል፡፡ ስለዚህ በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 98/1/ /ሠ/ መሠረት የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ እንዲሰረዝ ተወስኗል፡፡ ጉዳዩም በአቃቤ ሕግ በኩል ክስ ተመስርቶበት ይገኛል።
4. የተለያዩ ነጥቦች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ወይም ሰነዶችን አሟልተው እንዲያቀርቡ ተገልጾላቸው የማጣራት ሂደታቸው ካልተጠናቀቁት ፓርቲዎች መካከል የሚከተሉት ላይ ቦርዱ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
ሀ. በቂ ማብራሪያ በማቅረብ መስፈርቱ ሟሟላት አጠናቀው ምዝገባቸው የፀደቀ ፓርቲዎች
• ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ - 43%
• ሐረሪ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ሐዲድ/ (የመስራች ቁጥር የማይመለከታቸው አነስተኛ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ ፓርቲ)
• የመላው ኢትዮጵያዊያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) - 62%
ለ. የማጣራት ሂደታቸው የተጠናቀቀ ነገር ግን የቴክኒክ መስፈርቶች ይቀራቸው ከነበሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሂደታቸውን አሟልተው ያጠናቀቁና ተቀባይነት ያገኙ
• ህዳሴ ፓርቲ /ሕዳሴ/ - 100%
• የካፋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት /ካሕዴኅ/ - 71%
• የሲዳማ አንድነት ፓርቲ /ሲአፓ/ - 85%
ሐ. ከቦርዱ በተሰጠው አስተያየት መሠረት በሰነዶች ላይ ማስተካከያ ባለማድረግ የተሰረዘ
• የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ጉሕዴን/
መ. በፓርቲ አርማቸው ላይ ቅሬታ በመቅረቡ ለአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የኢትኖግራፊ የትምህርት ክፍል የባለሞያ ማብራሪያ የተጠየቀበት
• የራያራዩማ ፓርቲ
5. ከዚህም በተጨማሪ አፈጻጸሙ በተጀመረው የ6ተኛው አገራዊ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ መሳተፍ የሚችሉት ፓርቲዎች በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፉት 52 የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆናቸውን ቦርዱ ያሳውቃል። ለመሳተፍ ቅቡልነት ያላቸው እስከአሁን ያለውን ሂደት ያጠናቀው የጨረሱ ፓርቲዎች መሆናቸውን ያሳውቃል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም