የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎች የሥርዓተ-ፆታ ኦዲት ሪፖርት ዙሪያ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችለውን የምክክር መድረክ አካሄደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከተ.መ.ድ የሥርዓተ-ፆታ ዕኩልነትና ሴቶችን የማብቃት ክፍል ጋር በመተባበር በትላንት ዕለት ጥር 6 ቀን 2013 ዓ.ም የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ውብሸት አየለና የቦርዱ አመራር የሆኑት ብዙወርቅ ከተተ በተገኙበት በፖለቲካ ፓርቲዎች የሥርዓተ-ፆታ ኦዲት ሪፖርት ዙሪያ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችለውን የምክክር መድረክ አካሄደ። መድረኩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት የተገኙበት ሲሆን፤ የመድረኩን ዓላማና ከመድረኩ የሚጠበቀውን ውጤት በምርጫ ቦርድ የሥርዓተ- ፆታና ማኅበራዊ አካታችነት ኃላፊ የሆኑት መድኃኒት ለገሠ ማብራሪያ ሰጥተውበት ኦዲት ሪፖርቱ ቀርቧል።
የኦዲት ሪፖርቱን ዝርዝር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥርዓተ-ፆታና የሕግ ረ/ፕሮፌሰር የሆኑት እመዛት መንገሻ (ዶ/ር) አማካኝነት ቀርቧል። ዶ/ር እመዛት በንግግራቸው ጥናቱ ፓለቲካ ፓርቲዎች መሠረታዊ የሥርዓተ-ፆታ ዕኩልነት ለማረጋገጥና ሴቶችን ለማብቃት የሚያስችሉ ድንጋጌዎች በፓርቲዎቹ መርኃ-ግብርና የስትራቴጂ ዕቀዶች ውስጥ ተገቢውን ቦታ ተሰጥቷቸዋል ብሎ ለመናገር እንደማያስደፍር ገልጸው፤ ሚዲያዎችም ሴቶችንና ፓለቲካን የሚረዱበት አግባብ ሊሠራበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ዶ/ር እመዛትን ንግግር የሚጋሩት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ በበኩላቸው ሴቶችን በዕጩነት የሚያቀርብና ለአመራርነት የሚያበቃ አሠራር ፓለቲካ ፓርቲዎቹ መከተል እንደሚገባቸው የገለጹ ሲሆን፤ በመድረኩ የተገኙት ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የጥናቱን ግኝቶች ከግምት ውስጥ በከተተ መልኩ እንዲሆን ጠይቀዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች መሠል ጥናቶች ያላቸውን ትልቅ ፋይዳ ገልጸው፤ በጥናቱ ላይ ያላቸው ሀሳብና አስተያየት ሰጥተውበታል። ከመድረኩ ለቀረቡትን አስተያየቶች በዶ/ር እመዛት፣ በቦርዱ አባል ብዙወርቅ ከተተና በቦርዱ ስርአተጾታ እና አካታችነት ሃላፊዋ መድኃኒት ለገሠ መልስ ተሰጥቶባቸዋል። ቦርዱ ከዚህ ቀደም በኦዲት ሪፖርቱ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር እንደመከረበት ይታወሳል።