Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ቦርድ ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አደረገ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ታኅሣሥ 22 ቀን 2013 ዓ.ም በምርጫ ቦርድ ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አደረገ። መድረኩ የቦርዱ ሰብሳቢ የሆኑት ብርቱካን ሚደቅሳ ባደረጉት ንግግር የተከፈተ ሲሆን፤ በንግግራቸውም የፓርቲዎቹን መገኘት አመስግነው፤ ፓርቲዎቹ በረቂቅ መመሪያዎቹ ላይ የላቸውን ገንቢ አስተያየቶች እንዲያካፍሉ ጥሪ አድርገዋል። ረቂቅ መመሪያዎቹ ቦርዱ በኢትዮጲያ የምርጫ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 3 እና አንቀጽ 57 ንዑስ አንቀጽ 4 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፤ የድምፅ አሰጣጥን፣ ቆጠራንና የምርጫ ውጤት አገላለጽ ሂደት አፈጻጸምን ግልጽና ቀልጣፋ ለማድረግ፤ እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚዎች ፣ የዕጩ ወኪሎች፣ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች፣ የሀገር ውስጥና የዓለም ዐቀፍ ታዛቢዎች በነዚኽ ሂደቶች ላይ ወጥነት ያለው አሠራር እና በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል ተብሎ የረቀቁ ሲሆን፤ ይኽንንም የመድረኩ አቅራቢ የሆኑት ጌታቸው አሰፋ (ዶ/ር) ሰፊ ማብረሪያ ሰጥተውበታል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የገቢ፣ የወጪና የንብረት አስተዳደር እና ሪፖርት አቀራረብ መመሪያና የድጋሚ ምርጫ አፈጻጸምን የተመለከቱት ረቂቅ መመሪያዎችን ጨምሮ የመድረኩ አቅራቢ በሆኑት ባለሞያዎች ጌታቸው አሰፋ (ዶ/ር)፣ ሰለሞን ግርማና ዳኛቸው መለሰ ማብራሪያ የተሰጠበት ሲሆን፤ ማብራሪያዎቹን ተከተሎ በሁለት ዙር ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጋር የቦርዱ አመራር በሆኑት አቶ ውበሸት አየለ መድረክ መሪነት የፓርቲ ተወካዮቹ ሀሳብና አስተያየት እንዲሰጡበት ተደርጓል ፓርቲዎቹም እንዲብራራላቸው የፈለጉትን አንቀጽና ቢጨመር ያሉትን ሀሳብ ያጋሩ ሲሆን፤ ባለሞያዎቹ የፓርቲ ተወካዮቹ ባቀረቧቸው አስተያየቶች መሠረት ማብራሪያ ሰጥተውበታል። ፓርቲዎቹ የሚኖራቸውን አስተያየቶች በመድረኩ ሣይወሰኑ በጽሑፍም ማቅረብ እንደሚችሉ ባለሞያዎቹ ገልጸዋል።

Share this post