በምርጫ መታዘብ ሥራ መሳተፍ ለሚፈልጉ የአገር ውስጥ ሲቪል ማህበረሰብ

ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረበ ጥሪ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢፌዴሪ ህገመንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና ቦርዱን ባቋቋመው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ ምርጫ ለመታዘብ ለሚፈልጉ የአገር ውስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ መስጠት እና መከታተ የሚያስችለውን መመሪያ አርቅቆ፣ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ወኪሎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ያገኘውን ግብዓት በማካተት፣ የአገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች ፈቃድ አሰጣጥ እና የሥነ ምግባር መመሪያ ቁጥር 05/2012ን አፅድቋል፡፡

በዚሁም መሰረት በቀጣዩ 6ኛው አጠቃላይ ምርጫ  የአገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች መሳተፍ ነፃ፣ፍትሃዊ እና ገለልተኛ ምርጫ እንዲኖር በማድረግ ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ በማመን፣6ኛውን የሀገር-አቀፍ አጠቃላይ ምርጫ መታዘብ ሚፈልጉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥያቄያቸውን ለቦርዱ እንዲያቀርቡ ይህንን ጥሪ ማድረግ አስፈልጓል፡፡ በዚህ መሠረት፡-

  • ለትርፍ ያልተቋቋማችሁ፣ የመንግስት አካል ያልሆናቸሁ እና በህግ ተመዝግባችሁ የምትንቀሳቀሱ፣

  • ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት ነጻ የሆናችሁ፤

  • የተቋማችሁ የቦርድ አባላት እና መሪዎች የማንኛውም የፓለቲካ ድርጅት አባል ያልሆኑ

  • የምርጫ መታዘብን ሥራ ለመወጣት የሚያስችል ብቃት ያላችሁ እና የምታሰማሯቸው ታዛቢዎች ምርጫን በገለልተኝነት ለመታዘብ የሚችሉ፤ እንዲሁም

  • ለምርጫ መታዘብ ሥራ በመመሪያው የወጡ ሌሎች መስፈርቶችን የምታሟሉ እና ምርጫ ለመታዘብ የምትፈልጉ

አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለዚሁ የተዘጋጀውን  የማመልከቻ ቅጽ፣ የታዛቢዎች ዝርዝር መረጃ ቅጽ እና ቃለ መሃላ  በመሙላት የተጠየቁ ሰነዶችን በማያያዝ ማመልከቻችሁን ዋናው መ/ቤት፣ ለምርጫ ቦርድ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ወይም በኢሜል አድራሻችን externalrelations [at] nebe.org.et () ይህ ማስታወቂያ በመገናኛ ብዙሀን ከወጣበትቀን ከታህሳስ 02 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ 15 የስራ ቀናት ውስጥ  እንድታቀርቡ ቦርዱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የማመልከቻ ዝርዝር ቅጾቹን ከቦርዱ ድረ ገጽ  www.nebe.org.et ፣ ከስር በተያያዙት ማስፈንጠሪያዎች ወይም ከቦርዱ ዋና ጽህፈት ቤት እና የክልል ጽህፈት ቤቶች በግንባር መውሰድ እንደምትችሉ እያሳወቅን ከዚህ በፊት ጥያቄ ያቀረባችሁ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ማመልከቻችሁን በመመሪያው እና ጥሪው ላይ በተዘረዘረው መሠረት አገናዝባችሁ እና አሟልታችሁ ድጋሚ ማቅረብ እንደሚገባችሁ በዚህ አጋጣሚ እናሳውቃለን፡፡

የሀገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች ፈቃድ አሰጣጥ፣ አሠራር እና ስነ ምግባር መመሪያ

የምርጫ መታዘብ ፈቃድ ለማግኘት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  የሚቀርብ ማመልከቻ 

የምርጫ መታዘብ ፈቃድ እንዲሰጠው በጠየቀ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት  የበላይ ኃላፊ የሚሞላ ቃለመሃላ 

የታዛቢዎች ዝርዝር መረጃ ቅጽ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

 

የጥሪ ማስታወቂያ
ታህሳስ 02 ቀን 2013 ዓ.ም