የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለተከታታይ ቀናት ሲያደርገው የነበረው ምክክር ተጠናቀቀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለተከታታይ ሶስት ቀናት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሲያደርግ የነበረውን ውይይት ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም አጠናቋል፡፡ በውይይቱ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች፣ የሚዲያ ማህበረሰብ አባላት እና የፓለቲካ ፓርቲዎች ተገኝተዋል፡፡ በምክክር መድረኩ የተነሱ ዋና ዋና ጉዳዮች የኮቪድ ወረርሽኝ ውስጥ በሚደረግ ምርጫ ዋና ዋና ዝግጅቶች ምን ይመስላሉ? ከባለድርሻ አካላት ምን ይጠበቃል? የቦርዱስ ዝግጅት ምን ይመስላል? ዋና ዋና የምርጫ ተግባራት መቼ ይደረጋሉ? የምርጫ የጸጥታ ችግሮችስ እንዴት መታየት አለባቸው የሚሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
ቦርዱም በበኩሉ በኮቪድ ውስጥ ምርጫ ማካሄድ ዝግጅቶችን፣ ዋና ዋና የምርጫ ተግባራት እና የሚፈጸሙበት ጊዜን እና የምርጫ ጸጥታን የተመለከቱ እቅዶቹን ይፋ አድርጓል፡፡ ፓለቲካ ፓርቲዎች በተለይ በኢትዮጵያ ባለው የጸጥታ ችግር የተነሳ ምርጫን ማድረግ አስቸጋሪ ይሆናል የሚል ስጋቶቻቸውን ገልጸዋል፡፡ ቦርዱም በበኩሉ ሙሉ የጸጥታ እቅድ በማውጣት እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የመስራት እቅዱን ለባለድርሻ አካላቱ አጋርቷል፡፡ ውይይቱን ቦርዱ አመራር አባላት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ውብሸት አየለ፣ ብዙወርቅ ከተተ እና አበራ ደገፋ (ዶ/ር) የመሩት ሲሆን ከምክክር መድረኩ የተገኙትን ግብአቶች በማካተት ቦርዱ የሚቀጥሉትን ተግባራት እና ሊከናወኑ የሚችሉባቸውን ጊዜዎች የሚያሳውቅ ይሆናል፡፡
ተጨማሪ ምስሎችን ለማግኘት የምስል ክምችት ገጽ ይጎብኙ!
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ