Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስለመጪው አገራዊ ምርጫ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለመጪው አገራዊ ምርጫ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን አስመልክቶ ባሳለፍነው ሳምንት ከመንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ ወቅት የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች ሚኒስትሮች የተገኙ ሲሆን ከእያንዳንዱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የሚጠበቁ ዋና ዋና ትብብሮች ምን መሆን እንዳለባቸው ውይይት እና ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ተቋማት የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር፣ ሰላም ሚኒስቴር፣ መከላከያ ሚኒስቴር፣ ሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርን እና የማእከላዊ ስታቲስቲክስ ባለስልጣን ሲሆኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይቱን አስተባብሯል፡፡ በውይይቱ መሰረትም

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የገንዘብ ሚኒስቴር - በኮቪድ ወረርሽኝ ውስጥ የሚከናወን ምርጫ በመሆኑ የሚያስፈልገውን ተጨማሪ በጀት በወቅቱ መልቀቅ፤ እና ለምርጫ አስፈጻሚዎች የግል መከላከለያ ቁሳቁሶች (PPE) ግዥ እና አቅርቦትን አስመልክቶ ልዩ እገዛ ማድረግ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የጤና ሚኒስቴርን - ቦርዱ ኮቪድ19ን ለመከላከል ሊወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎችን ግምገማ ማድረግና ሞያዊ አስተያየት መስጠት፤ ቦርዱ ምርጫና ኮቪድ19ኝን አስመልክቶ ለሚያወጣቸው መመሪያዎች እና የአስራር መግለጫዎች ሞያዊ ግብአት መስጠት፣ የወረርሽኙን ዝርዝር አገራዊ እና ክልላዊ ሁኔታ ስብጥር እንዲሁም ተጋላጭነት የሚያሳይ ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለቦርዱ መስጠት፤ እንዲሁም በምርጫው ሂደት ወቅት የሚፈጠሩ የወረርሽኙን ተጋላጭነት ለመቀነስ የጋራ አሰራር ስርአትን ከቦርዱ ጋር በመሆን መቀየስ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሰላም ሚኒስቴር - የምርጫ ጸጥታ ስጋቶች የሚገመገሙበትን የጋራ መድረክ ማዘጋጀት፤ ከፓለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን በጋራ የመፍታት ስርአት መፍጠር፤ የህግ አስፈጻሚ አካላት በምርጫ ወቅት ሊኖራቸው ስለሚገባ ስነምግባር፣ አቅም ግንባታ ስልጠና አሰጣጥ በጋራ መስራት፤ ለምርጫ ኦፕሬሽን አስፈላጊ እና ወቅታዊ የሆኑ መረጃዎች እና አቅጣጫዎች ለቦርዱ መስጠት፤ እንዲሁም የአካባቢያቸው የተፈናቀኑ ዜጎችን ወቅታዊ መረጃ ለቦርዱ መስጠት

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሚኒስቴር - ልዩ የምርጫ ጣቢያ ለማቋቋም የሚያስችል መረጃዎችን ማቅረብ፤ አስፈላጊ የሆኑ የሎጄስቲክስ እና የጸጥታ አገልግሎት መስጠት፣ የጸጥታ ችግር ባለባቸው ልዩ ቦታዎች ለምርጫ ኦፕሬሽን አስፈላጊ የሆነ ልዩ የጸጥታ ማስጠበቅ ድጋፍ ማድረግ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር- በየትምህርት ተቋማቱ የሚገኙ ለመራጮች ምዝገባ፣ ለድምጽ አሰጣጥ የሚያገለግሉ የተማሪዎች መረጃን መስጠት

የማእከላዊ ስታቲስቲክስ ባለስልጣን - የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ እና ስምሪት ሂደት የሚያግዙ መረጃዎችን፣ ተሞክሮዎችን ማጋራት እንዲሁም በመላ አገሪቱ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች፣ አስተዳደራዊ ለውጦች እንዲሁም አዳዲስ የስነህዝብ መረጃዎች ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ማጋራት ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ናቸው፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረበለትን የህዝበ ውሳኔ ማደራጀት ጥያቄ አስመልክቶ ተጨማሪ መረጃዎችን እና ማብራሪያዎችን ምክር ቤቱን ጠይቋል፡፡ እነዚህም ፌዴሬሽን ምርክ ቤት ጥያቄው የቀረበበትን እና ሌሎች ውሳኔ ለመስጠት ሊረዱ የሚችሉ ሰነዶችን እና መረጃዎችን እንዲሁም የህዝቡ ፍላጎት እንዲመዘን የተጠየቀው በእያንዳንዱ ዞን እና ልዮ ወረዳ ወይስ በጥቅል መሆኑን በማረጋገጥ ለቦርዱ እንዲገልጽ ሲሆን፣ እነዚህን መረጃዎች መሰረት አድርጎ ቦርዱ ውሳኔ የሚያሳልፍ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

Share this post