የውይይት መድረክን ስለመሰረዝ
ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔን ሲያከናውን ዋና ዋና ከሆኑት የምርጫ ተግባራት መካከል አንዱ የሆነውን መራጮች የሚገባውን መረጃ እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን የምርጫ ቅስቀሳ ቀናት አሳውቆ እንደነበር ይታወቃል። ከዚህም በተጨማሪም ለሲቪል ማህበራት እና ለፓርቲዎች ጥሪ በማድረግ አስፈላጊውን የቅስቀሳ መድረክ እንደሚያዘጋጅ ገልጾ እንደነበርም ይታወሳል።
የተመደቡት የቅስቀሳ ቀናት መድረሳቸውን ተከትሎ ቦርዱ የሚያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዝርዝር ሁኔታ ላይ ከሚመለከታቸውና ለመሳተፍ ከተመዘገቡ አካላት እንዲሁም ከሚዲያዎች ጋር ተነጋግሮ ውይይት ቢያደርግም ከሲዳማ ዞን አመራር አካላት እና በዞኑ በሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በኩል ተሳትፎ ለማድረግ ፍቃደኛነት ባለመኖሩ ሚዛናዊ ውይይት መድረክ ማዘጋጀትን አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎታል። በመሆኑም ሚዛናዊነቱ ያልተረጋገጠ መድረክ ማዘጋጀት ከቦርዱ መርሕ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ የውይይት መድረኩን ለመሰረዝ ተገዷል። ቦርዱ በሚያከናውናቸው ማንኛውም ምርጫዎች ውስጥ መራጮች በቂ መረጃ የማግኘት መብታቸው መከበሩን ለማረጋገጥ የሚሠራ ሲሆን ይህንንም በተቻለው መጠን በሚደረጋቸው ማንኛውም ምርጫዎች ውስጥ ለመተግበር ጥረት እንደሚያደርግ ለመግለጽ ይወዳል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ