የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በምርጫ ጊዜ የሚነሱ አለመግባባቶችና ክርክሮች አፈታትን በማስመልከት አውደ ጥናት አያካሄዱ
የካቲት 28 ቀን 2012 ዓ.ም.
የአውደ ጥናቱ ዓላማ በመጪው ነሐሴ በሚከናወነው አገር አቀፍ ምርጫ ወቅት ፍርድ ቤቶች የሚኖራቸው ሚና እና የህግ ማእቀፎቹን ማስተዋወቅ እንዲሁም ከዳኞች ጋር ምክክር ማካሔድ ነው፡፡ አውደጥናቱን የከፈቱት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት መአዛ አሸናፊ ሲሆኑ በንግግራቸውም የድምፅ ቆጠራ እና የምርጫ ውጤት ጋር የተገናኙ ክርክሮች መጨረሻው ውሳኔ ሰጪ አካል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሆኑን አስታውሰው፣ በምርጫ ሂደቱ ወቅት ለሚኖሩ የፍትህ ሂደቶችም ልዩ የምርጫ ችሎት ማደራጀት ላይ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ በበኩላቸው ፍርድ ቤቶች በገለልተኝነት ምርጫን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የማየት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ እምነት እንዳላቸው ገልጸው ቦርዱም ይህንን ጥረት ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አውደጥናቱ ሙሉ ቀን የሚቆይ ሲሆን፦
• የምርጫ ክርክር ሂደት እና ህጋዊ ማእቀፉ፣ የመረጃ ልውውጥ አስፈላጊነት፣
• ከደቡብ አፍሪካና ከኬንያ የምርጫ ክርክር ሂደቶች ተሞክሮዎችን መጋራት እንዲሁም በምርጫ ጉዳዮች ላይ የተፋጠኑ ውሳኔዎችን ለመስጠት የሚያስፈልጉ ሁኔታዎች ላይ፣
• በምርጫ ሂደት የሚከሰቱ አለመግባባቶች እና ክርክሮችን በመፍታት ሂደት- የጊዜ ሰሌዳ ፣ የሚመለከታቸው አካላት ስልጣን እና አቤቱታ አፈታት ዙሪያ አዋጅ 1162/2011 በማስተዋወቅ ላይ አተኩሮ ይወያያል፡፡