Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጪውን አገራዊ ምርጫ እና የጊዜ ሰሌዳ አስመልክቶ የምክክር ውይይት አደረገ

ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም.              

ውይይቱ የቦርዱ የኦፕሬሽን እቅድና የ2012 የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ያተኩራል።

ውይይት እየተደረገበት ያለው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ይህንን ይመስላል፣ ፓለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስተያየትና ግብአት ይሰጡበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በምርጫ የጊዜ ሰሌዳው እና አፈፃፀሙ ላይ ውይይት እየተካሄደ ሲሆን የተነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎች እና አስተያየቶች፦
1. የመራጮች ምዝገባ ጊዜ 30 ቀናት ያንሳል፣
2. የእጩ ምዝገባ ቀናት አንሷል፣ ቢታሰብበት፣ 
3. ቀኑ ክረምት ላይ በመዋሉ ለማስፈፀም ያስቸግራል፣ ጥቅምት/ኅዳር ላይ ለምን አይሆንም?፣
4. በምርጫ ዘመቻ ወቅት ወከባ እንዳይፈጠር ቦርዱ ዝግጅት ቢያደርግ?፣
5. የምረጡኝ ቅስቀሳ ቀናት ያንሳሉ፣ ከአሁን ጀምሮ ቅስቀሳ የጀመሩ ፓርቲዎችም አሉ፣ ቦርዱ ምን ይላል?፣
6. ፓርቲዎች የድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ የሚደረደሩበት ቅደም ተከተል በእጣ ይሆናል ማለት ምን ማለት ነው?

በቦርዱ አመራር አካላት የተሰጡ መልሶች፦
1. የመራጮች ምዝገባ በህግ የተቀመጠ 30 ቀን ነው።
2. የእጩ ምዝገባ ቀናት በህግ የተቀመጠ መልኩ ይታያል፣ አስፈላጊ ከሆነ ቀናት መጨመሩን ቦርዱ ሊያየው ይችላል ግን በእቅዱ ላይ የተቀመጠው ቀን ለፓርቲዎች አያንስም እንደውም ጫና የሚሆነው ቦርዱ ላይ ነው።
3. ነሐሴ ላይ ምርጫው መካሄዱ ቦርዱ ወዶ የገባበት አይደለም፣ ግንቦት ለማድረግ ስላልተቻለ ነው፣ ብዙ የተዘረዘሩ ለውጦች እያደረገ እንደሆነ ቦርዱ ገልፇል ስለዚህ ግንቦት ላይ ማድረግ የሚቻል አይደለም። አፈፃፀሙ ክረምት በመሆኑ ብዙ ችግር እንደሚገጥመው እሙን ነው ከክልል መንግሥታት፣ ከፌደራል መንግሥትና ሌሎች ተቋማት ቦርዱ የሎጀስቲክስ ድጋፍ ጠይቆ ለማስፈፀም ጥረት ያደርጋል። ከመስከረም ካለፈ ደሞ የህግ ጥሰት ይፈጥራል ስለዚህ ወደ ፊት መግፋት አልተቻለም።
4. የዘመቻ ጊዜ ከወከባ እና ችግር እንዳይኖር ቦርዱ ጥረት ያደርጋል፣ ከዚህ በፊት ፓርቲዎች ችግር ሲገጥማቸው ቦርዱ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፣ አሁን ይህንን ድጋፍ ለማስፋት በምርጫ ዘመቻ ወቅት የራሱ ዴስክ አዘጋጅቶ ተቋማዊ ድጋፍ ያደርጋል።
5. የምረጡኝ ቅስቅሳ አሁን መጀመር አይችልም፣ የተሰጠው ሦስት ወር በላይ ግን በቂ ነው፣ ከአሁኑ ቅስቀሳ የጀመሩ አሉ ለተባለው ውይይት እና ንግግር ከሕዝብ ጋር ማደረግ ይቻላል፣ እኔን ምረጡኝ የሚል ዘመቻ ግን መጀመር አይቻልም፣ ያንን የሚያደርጉ ፓርቲዎች ላይ ቦርዱ ማጣራት ያደርጋል።
6. ፓርቲዎች የድምፅ መስጫ ወረቀት ቅደም ተከተል ሲባል የሚደረደሩበት መንገድ በእጣ የሚወሰን ይሆናል እንጂ ከዚህ በፊት እንደነበረው አይሆንም። እጣው ላይ በሚደርሳቸው ቅደም ተከተል መሠረት ፓርቲዎች የድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ በቅደም ተከተል ይቀመጣሉ።

 

Share this post