Skip to main content

ኢትዮጵያ የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግ ረቂቅ አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቀርቦ ውይይት ተደረገበት

ሐምሌ 10 ቀን 2011 ዓ.ም.

በአገራችን የምርጫ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ቅሬታ ሲቀርብባቸው ከነበሩ ህጎች መካከል አንደኛው የምርጫ ህጉ እንደሆነ ይታወቃል። የኢ.ፌ.ድ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያቋቋመው የህግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔና ጉባኤው የዲሞክራሲ ተቋማትን በተመለከተ ኃላፊነት የሰጠው የሥራ ቡድን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር የምርጫ ህጉን የተመለከቱ የህግ ማሻሻያ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል።። በኢትዮጵያ ባጠቃላይ ሦስት ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመለከቱ አዋጆች የነበሩ ሲሆን እነሱም የኢትዮጵያ የምርጫ ህግ አዋጅ ቁጥር 532/1999፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ሥነ ምግባር ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 662/2002 ናቸው። ከነዚህ ህጎች ውስጥ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጠንካራ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ የሆነ የምርጫ አስፈፃሚ ተቋም ሆኖ እንዲደራጅ ለማድረግ በተሰራው ሥራ ከአዋጅ ቁጥር 532/1999 ውስጥ የቦርዱን መቋቋም፣ ሥልጣንና ተግባሩን፣ የአባላቱን አሰያየምና አነሳስ እንዲሁም የቦርዱን አሠራር የሚመለከቱትን አንቀጾች በማሻሻል የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ወጥቷል።

ቀሪዎቹ ህጎች ላይ የዲሞክራሲ ተቋማት የሥራ ቡድን ጥናት በማድረግ ማሻሻያ ሊደረግባቸው የሚገባቸውን ጉዳዮች ከለየ በኋላ ህጎቹ በአንድ አዋጅ ተጠቃለው ቢወጡ ላፈጻጸማቸውም ሆነ ለተደራሽነታው ያለው ጠቃሚነት የላቀ መሆኑን ለባለድርሻ አካላት ያቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት በማግኘቱ የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግ ረቂቅ አዋጅ ሊዘጋጅ ችሏል። የሥራ ቡድኑ የምርጫ ሥርዓትን፣ የምርጫ አፈጻጸምን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሰራረት እና አስተዳደርን፣ የምርጫ ሥነ ምግባርን፣ የምርጫ ታዛቢዎችን፣ የሥነዜጋ ትምህርትን እንዲሁም በምርጫ ወቅት የሚነሱ ክርክሮችን የተመለከቱ ጥናቶችን አድርጓል። ጥናቶቹም በኢትዮጵያ የሚገኙ ህጎችን በሀገሪቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ፣ ባለማቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን ካገኙ መለኪያዎች እና በተመሳሳይ ሁኔታ ባሉ ሐገሮች ካሉ ልምዶች አንጻር በመፈተሽ ያሉባቸውን ችግሮች በመንቀስ አውጥተዋል። የጥናት ግኝቶቹንም ለባለድርሻ አካላት በማቅረብ ግብዓቶች ተሰብሰበዋል። በመቀጠልም የሥራ ቡድኑ በጥናቶቹና ከውይይት መድረኮች በተገኙ ግብዓቶች ላይ በመመሥረት ሁሉንም ምርጫንና ፖለቲካ ፓርቲዎችን የተመለከቱ ጉዳዮችን ያካተተ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጀቷል፡፡ የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ ለመገምገምና ለማዳበር ከቦርዱ፣በሀገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በጉዳዩ ላይ ሰፊ ልምድና እውቀት ካላቸው የውጭ ሀገር ባለሞያዎች ጋር ምክክር አድርጓል። ግብዓቶቹን በማካተትም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ ተዘጋጅቷል። በረቂቁም ላይ ከቋሚ ኮሚቴው ጋር ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።

Share this post