Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዳዲስ የቦርድ አባላት ሹመት

ሰኔ 8 ቀን 2011 ዓ.ም.  

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትላንትናው ዕለት በቅርቡ በጸደቀው አዋጅ 1133/2011 መሠረት አራት ተጨማሪ የቦርድ አባላትን ሾሟል። የቦርድ አባላቱ ምልመላ ሂደትን ለማስተባበር ሰባት አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት መልማይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ተግባር መግባቱ ይታወሳል። በዚህ መሠረትም መልማይ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ዕጩ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት መልማይ ኮሚቴ የውስጥ አሰራር መመሪያ በማውጣት፣ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እጩ ቦርድ አባልነት ጥቆማ ሂደት ከሃያ በላይ በሚሆኑ የመገናኛ አውታሮች ለሕዝብ እንዲገለፅ በማድረግ፣ 200 ጥቆማዎች በስልክ፣ በኢ-ሜይል፣ በአካል እና ፋክስ አማካኝነት ተቀብሏል፡፡ የቀረቡት 200 ተጠቋሚዎችም በሦስት የማጣሪያ ምዕራፎች እንዲያልፉ አድርጓል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ በአዋጁ አንቀፅ 6 የተጠቀሱትን መሠረታዊ ተፈላጊ መስፈርቶች ማለትም ኢትዮጵያዊ ዜግነት፣ የትምህርት መስካቸው በአዋጁ የተጠቀሱት ስለመሆናቸው (በህግ፣ ፖለቲካል ሳይንስ፣ የሕዝብ አስተዳደር፣ ስታትስቲክስ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በሌሎች ከምርጫ ጋር ተያያዥ የሆኑ መስኮች)፣ በሥራ ዘርፉ ብዙ ተቋማት ውስጥ ስለመስራታቸው፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ስላለመሆናቸው፣ እንዲሁም ፍቃደኝነታቸውን በማረጋገጥ ከቀረቡት እጩዎች መካከል 20 የሚሆኑት ወደ ሁለተኛው ማጣሪያ እንዲያልፉ ተደርጓል። በሁለተኛው ማጣሪያ ደግሞ የተጠቋሚዎች የትምህርት ዝግጅት እና የሙያ ስብጥር፣ በዘርፈ ብዙ መድረኮችና ተቋማት ስለማገልገላቸው እንዲሁም በተነፃፃሪነት ገለልተኛ በሆኑ ተቋማት ውስጥ ስለመስራታቸው፣ በተቻለ አቅም የብሔር፣ የፆታ ስብጥርን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከ20 ዕጩዎች ውስጥ፣ 10 ዕጩዎች ለሦስተኛው የማጣሪያ ምዕራፍ እንዲሻገሩ ተደርጓል።

በሦስተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ፣ የመልካም ሥነ-ምግባር እና ስብዕናቸው፣ ኃላፊነት የመሸከም ብቃታቸው፣ ሀሳብን የመግለፅ ችሎታቸው፣ ለምርጫ ቦርድ ተቋማዊ ለውጥ ያላቸው ራዕይ እና ሀገራዊ ምልከታን እንዲሁም የቡድን ሥራ ልምዳቸውን መሠረት በማድረግ ላለው አራት(4) ክፍት ቦታ ለእያንዳንዱ ሁለት(2) ሁለት(2)፣ በጠቅላላው ስምንት(8) እጩዎችን ኮሚቴው ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አቅርቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልማይ ኮሚቴው አጠቃላይ አካሄድ እና ስለደረሰበት ደረጃ በኮሚቴው የቀረቡትን የመጨረሻ 8 ዕጩዎች በተመለከተ ከ20 በላይ የፓርቲዎች አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ የመልማይ ኮሚቴውን የመጨረሻ ዕጩዎች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የተሰጠውን ግብዓት መሠረት በማድረግ የሚከተሉትን አራት ዕጩዎች ለተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ተሹመዋል፡፡

1. ብዙወርቅ ከተተ

ትምህርት ደረጃ፦ በሥነ- ቋንቋ የማስተርስ ዲግሪ (የፍልስፍና እና የሕዝብ አስተዳዳር ትምህርት ያካተተ)
የሥራ ልምድ፦ በአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ በአክሽን ኤይድ ኢንተርናሽናል በለንደን፣ በኢትዮጵያ እና በሩዋንዳ ቢሮዎች፣ ሴፈር ወርልድ ምስራቅ አፍሪካ፣ አደጋ መከላከልና መልሶ ማልማት ላይ የሚሠራው የጀርመን አማካሪ ድርጅት እንዲሁም በአይርላንድ የልማት ድርጅት (አይሪሽ ኤድ) ውስጥ በኦፊሰርነት፣ በከፍተኛ የፕሮግራም ኃላፊነት፣ በዳይሬክተርነት እና በተለያየ ከፍተኛ ኃላፊነቶች ሰርተዋል፡፡
ብዙወርቅ የአማርኛ፣ የእንግሊዘኛ፣ የፈረንሳይኛ እና የስፓኒሽ ቋንቋዎችን ይናገራሉ፡፡

2. ውብሸት አየለ ጌጤ

የትምህርት ደረጃ፦ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ (ኤል.ኤል.ቢ)
የሥራ ልምድ፦ የረጅም ዓመት ልምድ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኝነት፣ በህግ ኤክስፐርትነት፣ የህግ አማካሪነት የሠሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የፍርድ ቤት ሥርዓት ማሻሻያ ምክር ቤት ሰብሳቢነት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ንግግር መድረክ አስተባባሪና አወያይነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ አቶ ውብሸት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ቃልኪዳን ሠነድ ሲፈረም በማዘጋጀትና በማወያየት ያስተባበሩ፣ ከተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በፍትህና የህግ ጉዳዮች ዙሪያ የሰሩ ባለሞያ ናቸው፡፡ ባለፉት ጥቂት አመታት በስዊድን አገር የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ በጎ አድራጎት ስራዎችንም ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡
አቶ ውብሸት የአማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው፡፡

3.ዶክተር ጌታሁን ካሳ

የትምህርት ደረጃ፦ በሕግ ትምህርት የዶክትሬት ዲግሪ
የሥራ ልምድ፦ በትግራይ ክልል አቃቤ ህግነት፣ በመቀሌ ዪኒቨርሲቲ በመምህርነት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ ቢሮዎች በአማካሪነት፣ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት (DFID, CAFOD, UNG international የመሳሰሉት)፣ ኢምባሲዎች እና የመንግሥት ተቋማት በአማካሪነት፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡ ከህግ ባለሞያነታቸው፣ አማካሪነታቸው እና መምህርነታቸው በተጨማሪ በአሁኑ ሰዓት በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ስር በሚገኘው የሕግ እና የፍትህ ጉዳዮች ማሻሻያ አማካሪ ጉባኤ ውስጥ አባል ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
ዶ/ር ጌታሁን የትግረኛ አማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው፡፡

4. ዶ/ር አበራ ደገፋ

የትምህርት ደረጃ፦ በሶሻል ዎርክ የዶክትሬት፤ በህግ እና የሰብዓዊ መብት የማስተርስ ዲግሪ
የሥራ ልምድ፦ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ከ20 ዓመት በላይ የማስተማር ልምድ ያላቸው፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመተባበር በርካታ የምርምር ሥራ ያካሄዱ፣ በላቀ የማስተማር ሥራቸው በ2009 ዓ.ም. ከዩኒቨርስቲው የሚሰጠውን “የላቀ የማስተማር አበርክቶት” ሽልማት ተሸላሚ ምሁር ናቸው፡፡
ዶ/ር አበራ የአፋን ኦሮሞ፣ የአማርኛ እና የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው፡፡
ከላይ ከቀረቡት እጩዎች መካከል አቶ ውብሸት አየለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመረጡ ሲሆን የተወካዮች ምክር ቤት አስቀድሞ የሾማቸው የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በምርጫ ቦርዱ መልሶ ማቋቋሚያ አዋጅ 1133/2011 አንቀጽ 28 መሠረት በሰብሳቢነታቸው እንደሚቀጥሉ በፓርላማው ውሳኔ ተመልክቷል፡፡

Share this post