ቦርዱ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን በመታዘብ ላይ ለተሠማሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሄደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከቦርዱ ዕውቅና አግኝተው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን በመታዘብ ሥራ ላይ ለተሠማሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባሳለፍነው ሣምንት መጠናቀቂያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሄደ። የመድረኩን የመክፈቻ ንግግር የቦርዱ ሰብሳቢ የሆኑት ሜላትወርቅ `ኃይሉ ያደረጉ ሲሆን፤ በንግግራቸውም ቦርዱ በቅድመ ምርጫ ተግባራቱ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ እንደነበር፤ ከዚኽም ውስጥ በምርጫ መታዘብ ሥራ ላይ ለሚሠማሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዕውቅና መስጠት አንዱ እንደሆነ አስታውሰው፤ ይኽም ከቅድመ ምርጫ እስከ ድኅረ-ምርጫ ያለውን ሦስቱንም የምርጫ ዑደቶች እንደሚያካትት ተናግረዋል።
የታዛቢዎች ተሣትፎ ለምርጫው ግልጽነት፣ አሣታፊነትና ተጠያቂነት ወሣኝ እንደሆነ፤ በዚኽም አግባብ የመራጮች ምዝገባ ሂደትን ተከትሎ ሪፖርት ላቀረቡት ድርጅቶች ምስጋናቸውን ገልጸዋልዋል። “መሰል ሪፖርቶች ከድምፅ መስጫው ቀን ቀደም ብለው መቅረባቸው የማስተካከያና የዕርምት ዕርምጃ ለመውሰድ ዕድል የሚሰጡ በመሆናቸው ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳላቸውና የመታዘብ ዐላማውም ይኽ ነው” ሲሉ አብራርተዋል። የማኅበራቱ ሪፖርት ለምርጫ ሥርዓቱ መዘመንና ለዲሞክራሲያዊነቱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው፤ ይኽም የበለጠ ትርጉም የሚኖረው ሕግን ተከትሎ ሲሠራ በመሆኑ፤ የዛሬው መድረክም ስለምርጫ የሕግ ማዕቀፍ፣ የታዛቢዎች መመሪያ ምን ይላል ስለሚለውና አጠቃላይ የምርጫ ዑደትን በተመለከተ፤ ከዚኽ በፊት በምርጫ መታዘብ ላይ ተሠማርተው ለሚያውቁት የበለጠ ትኩረት እንድትሰጡት እንዲሆን አዲስ ለተመዘገቡት ደግሞ ግንዛቤ ለመስጠት ታስቦ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የሰብሳቢዋን ንግግር ተከትሎ የቦርዱን አደረጃጀትና የምርጫን አጠቃላይ የሕግ ማዕቀፍ በተመለከተ የሕግ ባለሞያው አይተነው ደበበ፣ የምርጫውን ኦፕሬሽን በተመለከተ የቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ማስተባበሪያ ኃላፊ የሆኑት ቀነኒ ኢንሰርሙ፣ እንዲሁም የሪፖርት አቀራረብ አጠቃላይ ሂደት፣ የምርጫ ጣቢያ ደኅንነትና አካታችነትን በተመለከተ የቦርዱ የታዛቢዎች ምዝገባ እና ክትትል አስተባባሪ የሆኑት ናትናኤል መላኩ አማካኝነት ሰፊ ገለጻ ተሰጥቷል።
የባለሞያዎቹን ገለጻ ተከትሎ በርካታ ሃሳብና አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን፤ ከነዚኽም ውስጥ የፋይናንስ ውሥንነት፣ የምርጫ ጣቢያዎች ለመራጮች ያላቸው ምቹነት፣ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፣ የፀጥታ ሁኔታ ከተሣታፊዎች ከተነሡት ጥያቄዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።
ከተሣታፊዎች ለተነሡት ጥያቄዎች የቦርድ ሥራ አመራር አባል የሆኑት ነሲም አሊ በማጠቃለያ ንግግራቸው መልስ የሰጡ ሲሆን፤ በንግግራቸውም ከ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተወሰዱ ከሚባሉት ትልቅ ግብዓቶች ውስጥ የታዛቢዎች ሪፖርት በዋናነት ከሚጠቀሱት ውስጥ መሆኑንና ይኽም ለምርጫ ዐዋጁ መሻሻል እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀስ መሆኑን፤ ከዛም ባለፈ ቦርዱ የተለያዩ ፖሊሲዎችን ጭምር እንዲወጣ ምክንያት እንደሆኑ ተናግረዋል። ቦርዱ በቀሪ ቀናት ከተሣታፊዎች የተነሡ ጥያቄዎችን መልስ ለመስጠት የሚያስችል ሥራ እንደሚሠራና ሲቪል ማኅበራቱም በዛው ልክ ከነሱ የሚጠበቀውን ኃላፊነት እንዲወጡ ተናግረዋል።