የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሴት ፓለቲካ ፓርቲ እና የግል ተወዳዳሪ ዕጩዎችን ሥልጠና ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ተዓማኒና ሁሉን አካታች ለማድረግ የሚያስችለውን በርካታ የቅድመ ምርጫ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል። በዚኽም አግባብ ቦርዱ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ለሚወዳደሩ ሴት ፓለቲካ ፓርቲ እና የግል ዕጩዎች ሥልጠና ሰጥቷል።
ከሚያዝያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ምርጫ በሚደረግባቸው በ13 ክልሎችና በሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች በሚገኙ በ17 ከተሞች በተሰጠው ሥልጠና ላይ ከ1,731 በላይ ሴት ዕጩዎች የተሣተፉ ሲሆን፤ ዐላማውም ሴት ዕጩዎች በምርጫ ወቅት ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ፆታዊ ጥቃቶች መገለጫቸውና ምላሽ ስለሚሰጡበት ሕጋዊ አግባብ እንዲሁም የምርጫ ቅስቀሳ ላይ በሚኖራቸው ተሣትፎና የዐደባባይ ላይ ንግግሮችን ሲያደርጉ ሊከተሏቸው ስለሚገቡ ሥነ-ዘዴዎች ግንዛቤ እንዲያገኙ ማስቻል ነው።
በአዲስ አባባ የተካሄደውን ሥልጠና በንግግር ያስጀመሩት የቦርድ ሥራ አመራር አባሏ ነሲም አሊ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ባልተሣተፉበት ሁኔታ አንድን ምርጫ ፍትሐዊና አካታች ነው ማለት እንደማይቻል፤ ይኽንንም በማሰብ ቦርዱ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞችን ተሣትፎ ለማሳደግ በማሰብ በሕጎቹም ላይ ጭምር የሴቶችን ተሣትፎ ለመጨመር የሚያስችሉ ማበረታቻዎችን እንዲካተቱ እንዳደረገ ተናግረዋል። ሥልጠናው ሴቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ በሚኖራቸው ተሣትፎ በቂ ግንዛቤ አግኝተው ፖሊሲ ጭምር ማስቀየር የሚያስችላቸውን መቀመጫ እንዲያገኙ በማሰብ እንደተዘጋጀ ገልጸዋል።
ቦርዱ ከዩ.ኤን. ዉመን እንዲሁም ከአትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ጋር በመተባበር የሰጠው ይኽ ሥልጠና፤ የሴቶች ተሣትፎ አካታችነትን ተግባራዊ ከማድረግ ተለምዷዊ አጀንዳነት ባለፈ መለኪያውን ሴቶች ባላቸው ተሣትፎ ለዲሞክራሲ ግንባታ የሚኖራቸውን የላቀ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነው።