ተኽሊት ይመሰል


አቶ ተኽሊት በመንግሥት ሥራ (በሕዝብ አገልግሎት) ከ25 ዓመታት በላይ የካበተ ልምድ አላቸው፡፡ አቶ ተክሊት በነዚኽ ዓመታት የዐቃቤ ሕግ መመሪያ ኃላፊ፣ የከፍተኛ እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ፣ የሠበር ሰሚ ችሎት ዋና ሰብሳቢ ዳኛ፣ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባል፣ እንዲሁም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ አቶ ተክሊት በኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ የፍትሕ ሥርዓት እንዲሰፍን፤ ብሎም ጥራት ያለው ፍትሐዊ እና ውጤታማ የዳኝነት አገልግሎት እንዲሰጥ እና የዳኝነት ነፃነትን ከተጠያቂነት ጋር ሚዛኑን አስጠብቆ እንዲሠራ እንዲሁም በየደረጃው ያሉ ፍርድ ቤቶች ለፍትሕ መጠናከር ተቀናጅተው እና በትብብር እንዲሠሩ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡

አቶ ተክሊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥራ አመራር አባል ሆነው ከመሾማቸው በፊት ከፍርድ ቤት ሥራዎቻቸው በተጓዳኝ በሕግ ነክ ጉዳዮች በአሠልጣኝነት፣ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች የቡድን መሪ በመሆን ዘርፈ ብዙ ሥራ በመሥራት ፍሬያማ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡