Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዋና አሠልጣኞች ሥልጠና መስጠት ጀመረ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመሥክ አሠልጣኞችን በተዋረድ ለሚያሠለጥኑ ዋና አሠልጣኞች ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሥልጠና መስጠት ጀመረ። በትላንትናው ዕለት የካቲት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. የጀመረውንና በዛሬው ዕለት የሚጠናቀቀውን ሥልጠና የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ገለልተኛ እንዲሆን የምርጫ አስፈጻሚዎች ሚና የማይተካ በመሆኑ፤ ብቁ እና በሕግ መሠረት የሚሠሩ ምርጫ አስፈጻሚዎችን ለማብቃት የዋና አሠልጣኞች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ ዋና አሠልጣኞቹ በሁለቱ ቀናት የሚያገኙትን ሥልጠና በትኩረትና በኃላፊነት ስሜት ለመሥክ አሠልጣኞች ማስተላለፍ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

300 የሚሆኑት ዋና አሠልጣኞች በሥልጠናው ወቅት በምን አግባብ የማንዋል እና በቴክኖሎጂ የታገዘው የመራጮች ምዝገባ መከናወን እንዳለበት በዝርዝር የሚሠለጥኑ ሲሆን፤ በየሥልጠና ማዕከላቱ በመሠማራት ከ5,000 በላይ የመሥክ አሠልጣኞችን የሚያሠለጥኑ ይሆናል። የመሥክ አሠልጣኞችም በተዋረድ ከ214,000 በላይ ለሚሆኑ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች ሥልጠናውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Share this post