ቦርዱ ሐሰተኛና አደናጋሪ ምርጫ ነክ መረጃዎችን ለመከላከል የሚያስችለውን ብሔራዊ ትብብር ይፋ አደረገ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በያዝነው ሣምንት በምርጫ እና በድኅረ ምርጫ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ምርጫ ነክ ሐሰተኛና አደናጋሪ መረጃዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችለውን የብሔራዊ ትብብር ስምምነት ይፋ አደረገ። የይፋ ማድረጊያው መድረኩን የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በንግግር የከፈቱት ሲሆን፤ በንግግራቸውም የትብብር ማዕቀፉ ቦርዱ መጪው ምርጫ ነፃ እና ተዓማኒ እንዲሆን ምርጫ ነክ መረጃዎች ተዛብተው እና አሳሳች ሆነው ለኀብረተሰቡ እንዳይቀርቡና 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ተዓማኒነት ተጠብቆ እንዲከናወን ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራበት ነው ብለዋል።
ቦርዱ ምርጫን በገለልተኝነት፣ በነፃነትና በታማኝነት ለማካሄድ የተቋቋመ ሕገ-መንግሥታዊ ተቋም መሆኑን ያስታወሱት ሜላትወርቅ፤ የትብብር ስምምነቱ ቦርዱ ሐሰተኛ እና አደናጋሪ መረጃዎችን በመከላከል በምርጫው ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያደርሱ የሚያደርገውን ጥረት በእጅጉ እንደሚያግዝ ተናግረዋል። የብሔራዊ ትብብር ስምምነቱ ዐላማ በምርጫ ሂደት ሊሠራጩ የሚችሉ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለማጣራት፣ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት፣ መራጮች እና በምርጫው በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ድርሻ ያላቸውን ተቋማትና ግለሰቦች በተዛባ መረጃ ላይ ከተመሠረተ ውሣኔ አሰጣጥ እንዲጠበቁ ለማድረግና ምርጫው ነፃ እና ተዓማኒ መሆኑን ለማረጋገጥ ያለመ ነው።
ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (UNDP) ጋር በመተባበር በተዘጋጀው በዚኽ መድረክ ላይ የልማት ድርጅቱ የአፍሪካ ተወካይ የሆኑት ሳሙኤል ዶ (ዶ/ር) የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ የምርጫን ተዓማኒነት አደጋ ላይ ከመጣልም በተጨማሪ ግጭት የሚያስነሱ እንደሆኑ በመግለጽ፤ ኢትዮጵያ ለ7ኛ ጊዜ የምታካሂደው ጠቅላላ ምርጫ ተዓማኒነቱ የሚረጋገጠው በምርጫ ጣቢያ ከሚተገበረው የምርጫ ሂደት በተጨማሪ ለዜጎችና በምርጫው ተሣታፊ ለሆኑ ግለሰቦችና ተቋማት በሚደርሰው እውነተኛ የምርጫ መረጃ ነው ብለዋል።
በመድረኩ ላይ አጠቃላይ የብሔራዊ ትብብር ሥራው ዕቅድና ተጠባቂ ውጤትን የተመለከተ ገለጻ ተሰጥቶበታል። የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮዎችም ቀርበው እንዲሁ ውይይት ተደርጎባቸዋል።