Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአሜሪካ ሰብአዊ ተራድኦ-የምርጫ እና የፓለቲካ ሂደቶችን የሚያጠናክሩ የተለያዩ ድርጅቶች ጥምረት (USAID/CEPPS) እና ከአውሮፓ ህብረት-የአውሮፓ ምርጫ ነክ ሥራዎች ድጋፍ ማዕከል (EU/ECES) ጋር ውይይት አደረገ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአሜሪካ ሰብአዊ ተራድኦ-የምርጫ እና የፓለቲካ ሂደቶችን የሚያጠናክሩ የተለያዩ ድርጅቶች ጥምረት (USAID/CEPPS) እና ከአውሮፓ ህብረት-የአውሮፓ ምርጫ ነክ ሥራዎች ድጋፍ ማዕከል (EU/ECES) ጋር የኢትዮጵያን የምርጫ ሥርዓት ሂደት ለማሻሻል የተደረጉ ድጋፎች ያስገኙትን ጠቀሜታ እና በቀጣይ ሊሰጡ በሚገቡ የድጋፍ ማዕቀፎች ዙሪያ ከተቋማቱ አስተባባሪ አካላት ጋር ውይይት አደረገ፡፡ የውይይቱ ዋነኛ ትኩረት ቀደም ሲል በልማት አጋሮቹ ሲሰጥ ለነበረው ድጋፍ እውቅና ለመስጠት እና በቀጣይም አጋዥ ተቋማቱ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማበረታታት የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ነው።

በመርሃ ግብሩ የመክፈቻ መልዕክታቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ፤ግልፅ፣ ተዓማኒ እና ትክክለኛ ምርጫ ለማካሄድ በሚያደረገው ጥረት ቦርዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቋማዊ የማስፈፀም አቅሙን እያጎለበተ መጥቷል ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ይህ ተቋማዊ አቅምን እና የምርጫ ሂደትን ምቹ እና ዘመናዊ የማድረግ ትልቅ ሥራ ያለ እናንተ ስትራቴጂክ አጋርነት ሊሳካ አይችልም ብለዋል።

አጋር የልማት ተቋማቱ ላደረጉት እና በቀጣይ ለሚያደርጉት ሁለገብ ድጋፍ ምስጋናቸውን እና አድናቆታቸውን የገለፁት ወ/ሮ ሜላትወርቅ ቦርዱ በቀጣይ ከሁሉም የልማት አጋር ተቋማት ጋር ወጥ እና ቋሚ የግንኙነት ጊዜ የተቆረጠለት የጋራ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት መድረክ በማዘጋጀት ድጋፎቹ ያመጡትን ፋይዳ መገምገም፣ በሚገጥሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ በጋራ መምከር እና ፈጣን የእርምት ዕርምጃ መውሰድ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። በአሜሪካ ሰብአዊ ተራድኦ-የምርጫ እና የፓለቲካ ሂደቶችን የሚያጠናክሩ የተለያዩ ድርጅቶች ጥምረት (USAID/CEPPS) ከተሰጡ ድጋፎች መካከል በሺዎች ለሚቆጠሩ የክልል ምርጫ አስፈፃሚዎች፣ ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ ለምርጫ ጣቢያ የምርጫ አስፈጻሚዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት፣ በክልሎች የስነ-ዜጋ እና የመራጮች ትምህርትን ማስፋፋት፣ የክልል ምርጫ ማስተባበሪያ ቢሮዎች ያሉበትን ተቋማዊ ቁመና ለመለየት የዳሰሳ ጥናት ማካሄድ እና የኢትዮጵያ ፓለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን አቅም ማጎልበት ይገኙበታል።

በአውሮፓ ህብረት-የአውሮፓ ምርጫ ነክ ሥራዎች ድጋፍ ማዕከል (EU/ECES) ከተሰጡት እገዛዎች መካከል ለሀገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች ሥልጠና በመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎች እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ የምርጫ ቁሳቁሶች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የተጓጓዙበትን ወጪ መሸፈን፣ ምርጫ ነክ አለመግባባቶች በፍጥነት የሚፈቱበት ሥርዓት እንዲዘረጋ ብሎም የቦርዱን የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂክ ዕቅድ/ፓሊሲ የመቅረፅ ሥራን ማገዝን ያካተተ ነበር።

በውይይት መረሃ ግብሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በያዝነው ዓመት የሚያካሂደውን አካባቢያው ምርጫ እና በ2018 ዓ.ም የሚያስፈፅመውን 7ኛውን አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ ማዕከል አድርጎ፤ ከልማት አካል አጋራት የሚጠብቀውን የድጋፍ ፍላጎቶቹን በተመለከተ በወ/ሮ ሜላት ወርቅ ገለፃ አቅርቧል።

ቦርዱ እንዲደገፍ ከሚፈልግባቸው የድጋፍ አይነቶች መካከል፤ የምርጫ አስተዳደር ሂደትን ከማዘመን አኳያ የተለያዩ ሶፍትዌሮችን የማልማት፣ የታብሌት፣ የሰርቨር ድጋፎችን መሰል የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶችን የማግኘት፣ የሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና ሎሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በዲሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት በአግባቡ ተካተው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማገዝ፣ ሲቪክ ማህበራት የስነ ዜጋና መራጮች ትምህርት እንዲያስፋፉ፣ ምርጫ ነክ የክርክር መድረኮች እንዲያዘጋጁ እና በምርጫ ታዛቢነት እንዲሳተፋ በገንዘብ የመደገፍ፣ የፓለቲካ ፖርቲዎችን አቅም የማጎልበት እና የክልል ምርጫ አስተባባሪ ቢሮዎችን ጠንካራ መዋቅራዊ አደረጃጀት እንዲኖራቸው ማስቻል እና የመስሪያ ቁሳቁሶችን ማሟላት ይገኝበታል። በውይይት መርሃ ግብሩ ላይ ከተሳታፊ አካላት የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት እና ምላሽ ከተሰጠ በኃላ የውይይት መድረኩ ተጠናቋል።

Share this post