የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፓለቲካ ፖርቲዎች የሴቶች እና የአካል ጉዳተኞችን የፓለቲካ ውክልና ለማጎልበት የሚሰጣቸው የማበረታቻ (የፋይናንስ) ድጎማ የውጤታማነት ደረጃ በዳሰሳ ጥናት ተገመገመ
በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፖርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት ቦርዱ ለፓለቲካ ፓርቲዎች እያደረገ ያለው የማበረታቻ ድጎማ ከአካታችነት አንፃር ለታለመለት ዓላማ መዋሉን እና ያስገኘውን ውጤት ለመገምገም የሚያስችል በአማካሪ ባለሙያ በተጠና የዳሰሳ ጥናት ላይ የእውቅና (Validation workshop) አውደጥናት አካሄደ።
በአውሮፓ ህብረት፣ በኔዘርላንድ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ ኢንስቲትዩት እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድጋፍ በተዘጋጀው የዳሰሳ ጥናት የመጨረሻ የማዳበሪያ ግብዓቶች መሰብሰቢያ የእውቅና አውደጥናት ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን በአውደ ጥናቱ የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ "ሴቶችና የአካል ጉዳተኞችን በሀገራችን የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ የሕግ ማዕቀፎችን ማሻሻል እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በአሁኑ ወቅት የሴቶችና የአካል ጉዳተኞችን አካታችነች ለማረጋገጥ በቂ የሕግ ማዕቀፎች እና የስትራቴጂክ ዕቅዶች መኖራቸው ዕሙን ነው ያሉት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ውብሸት አየለ ሕጎቹን እና ዕቅዶቹን ከማስፈፀም አንፃር ግን ውስንነቶች አሉ ብለዋል።
የምርጫ ቦርዱ አባል ብዙወርቅ ከተተ በበኩላቸው የዚህ አውደ ጥናት ዋነኛ ዓላማዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓለቲካ ፓርቲዋች ሴቶችና አካል ጉዳተኞችን ለአባልነት፣ ለእጩነት እና ለአመራርነት እንዲያቀርቡ የሚሰጣቸው የማበረታቻ ድጎማ የታለመለትን ዓላማ አሳክቷል ወይ?፣ የፓለቲካ ፓርቲዎቹ ድጋፉን እንዴት ተጠቀሙበት?፤ የሌሎች ሀገሮች ልምድስ የኛን ነባራዊ ሁኔታ ከማሻሻል አኳያ ምን ትምህርቶች ልንቀስምበት እንችላለን እንዲሁም ከአፈፃፀም አኳያ ያሉብን የጋራ ተግዳሮቶቻችንን እንዴት ተቀናጅተን እንቅረፋቸው የሚሉ ናቸው ብለዋል።
የሥርዓተ ፆታ እኩልነት አቀንቃኞች እና ፓሊሲ አውጪዎች የሴቶች እና የአካል ጉዳተኞች በአንድ ሀገር የፓለቲካ ምህዳር ውስጥ የማሳተፍ ጉዳይ የፓለቲካ ፖርቲዋችን ይሁንታ እና ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ የተናገሩት የጥናቱ አቅራቢ ፍሬህይወት ስንታየሁ ( ዶ/ር) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች የፓለቲካ ተሳትፎቸው እና የአመራር ሚናቸው እንዲጎለብት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርገው የማበረታቻ የበጀት ድጎማ እስከነውስንነቱ አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል። የጥናት አቅራቢዋ ቦርዱ የሚሰጠው ድጋፍ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች በፓለቲካ ፖርቲዎች አደረጃጀት ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው እና የአመራርነት ሚናቸውን ለማረጋገጥ የድጋፉ ዓላማ በተጨባጭ እንዲሰምር የቁጥጥር እና የግምገማ ሥርዓቱን ማጠናከር እንደሚገባው ምክረ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።
በተጨማሪም አጥኚዋ የፓለቲካ ፖርቲዋቹም ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ትርጉም ያለው የፓለቲካ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ብቸኛው መግቢያ በር ስለሆኑ የፓለቲካ ፓርቲዎች አካታች አደረጃጀት፣ ግልፅ ፓሊሲ፤ሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን የሚያበቃ የሀብት አጠቃቀም ሥርዓት ሊኖራቸው እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።