Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ወቅት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ሊደግፉ ከሚችሉ ለጋሽ ድርጅቶች ጋር የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፥ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች የድጋፍ ፕሮገራሞችን ከሚመሩ አጋሮች እና ሌሎች ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶችን ከሚደግፉ አጋሮች ጋር ኅዳር 28 ቀን 2024 ዓ.ም. የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት አካሄደ።

የውይይቱ ዓላማዎች የሚከተሉት ነበሩ፡-

  • የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር አጋርነትን ለመቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት ለማረጋገጥ፤
  • እስከአሁን ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ያለውን አብሮ የመሥራት ልምድ ለማጋራት (በተለይ በስነዜጋ እና በመራጮች ትምህርት ፤ በምርጫ መታዘብ፤ የምርጫ ክርክሮችን በማዘጋጀት፤ በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብት ክትትል፤ እና በስርዓተ-ፆታ እና በማኅበራዊ አካታችነት ዙሪያ)፤
  • ስለ ምርጫ እንቅስቃሴዎች መረጃ ስለማጋራት እና
  • በዋናነት በጋራ እንደዚህ ዓይነት የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይቶችን በማሰቀጠል ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዘላቂ ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመወያየት ያለመ ነበር ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ክብርት ሜላትወርቅ ኃይሉ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም በዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት የምርጫ ወቅትን ጨምሮ፤ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች መራጮች በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምር እንዲያደርጉ፤ የስርዓተ-ፆታ እኩልነትን እና ማኅበራዊ አካታችነትን እንዲሁም አሳታፊነትን ከማረጋገጥም እና የምርጫ ሪፎርም እንዲደረግ የጉትጎታ ሥራ በመሥራት ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልፀዋል። በመቀጠልም የቦርዱ አባል ወ/ት ብዙወርቅ ከተተ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ካደረጉ በሗላ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይቱን ዓላማዎች ገልፀው፤ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዜጎችን ስለ መብቶቻቸው እና ስለግዴታዎቻቸው በማስተማር እና ተቛማትን ተጠያቂ በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልፀዋል።

በጠረጴዛ ዙሪያው ውይይት የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ምክር ቤት (Ethiopian CSO Council) እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ጥምረት ለምርጫ (Coalition of Ethiopian CSOs for Elections) ስለ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች የምርጫ ተሳትፎ እና በዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ስላላቸው ልምድ እንዲያካፍሉ እና ስለገጠማቸው ተግዳሮቶችም እንዲያጋሩ ተጋብዘው ሰፊ ውይይት ተደርጓል። ሁለቱም ጥምረቶች አስቻይ የሲቪክ ምህዳር አስፈላጊነትን፤ ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ ወሳኝነትን እንዲሁም በድጋፍ አድራጊ አጋሮች በኩል ቅንጅት እንዲኖር እና ድርርቦሽን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በውይይቱ 20 የድጋፍ ሰጪ አጋሮች የተሳተፉ ሲሆን፤ እነሱም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በመደገፍ ስለሚሠሯቸው ሥራዎች ገለፃ አድርገዋል።

አጠቃላይ ውይይቱን የመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ዶ/ር አበራ ደገፋ እና ወ/ት ብዙወርቅ ከተተ ሲሆኑ፤ በውይይቱ አፅንኦት ከተሰጣቸው ዋና ዋና ነጥቦች ውስጥ፡

  • የአካታችነትን ጉዳይ ማጠናከር
  • አስቻይ የሲቪክ ምህዳር መኖር አስፈላጊነት
  • የምርጫ ክትትል እና የምርጫ መታዘብ ሥራን ማስፋፋት እና ማጠናከር
  • የስነዜጋ እና መራጮች ትምህርት እንዲሁም የምርጫ መታዘብ ሰትራቴጂዎችን ማስፋፋት እና ማጠናከር፤
  • የምርጫ መረጃ በወቅቱ እና በበቂ ሁኔታ ማድረስ
  • ለምርጫ ታዛቢዎች እውቅና የመስጠት ሂደትን (accreditation) ማሳጠር እና ማሻሻል፤
  • በምርጫ ሥራ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የሚደግፉ አጋሮችን መለየት፤
  • ጥሩ አፈፃፀም ያላቸውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን መለየት እና ማበረታታት እና
  • የምርጫ ወቅት ብቻ ሳይጠበቅ ድጋፍ የማድረግ ወሳኝነት የሚሉት ይገኙበታል

በመጨረሻም እነደዚህ ዓይነት ውይይቶች እንዲቀጥሉ ተሳታፊዎች ተስማማተው ውይይቱ ተጠናቋል።

Share this post