ብዙወርቅ ከተተ
ብዙወርቅ ከተተ
በ1952 ዓ.ም. የተወለዱት ብዙወርቅ ከተተ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በግሪክ፣ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በኩባ ሐቫና ዩኒቨርሲቲ የውጪ ቋንቋዎች ትምህርት ክፍል በሥነ ቋንቋ የሁለተኛ ደረጃ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡
ወ/ሪት ብዙወርቅ፣ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰው በልዩ ልዩ ተቋማት ውስጥ ለ35 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከእነርሱም መካከል፥ የቀድሞው የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ አክሽን ኤይድ ኢንተርናሽናል (በለንደን፣ በኢትዮጵያ፣ በሩዋንዳ ካንትሪ ዳይሬክተር በመሆን)፣ በሴፈር ወርልድ የአፍሪካ ቀንድ ፕሮግራም አስተባባሪነት ይገኙበታል፡፡ በግጭት አፈታት እና መከላከል ላይ የሚሠራው የጀርመን አማካሪ ድርጅት ውስጥም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፕሮጄክት አስተባባሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ በአየርላንድ የረድኤት ድርጅት (አይሪሽ ኤይድ) ውስጥ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ፕሮግራም ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡
በተጨማሪም፣ ወ/ሪት ብዙወርቅ፣ ማኅበረሰባዊ ተሳትፎ በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ በመልካም አስተዳደር፣ በአቅም ግንባታ እና ሲቪክ ተሳትፎን በማበረታታት ላይ የሚሠራ፥ ዜጋ ለዕድገት የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራች እና የቦርድ ሊቀ መንበር ሆነው አገልግለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበራት ኅብረት (Union of Ethiopian Civil Society Organizations) የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራች እና የቦርድ አመራር በመሆን አገልግለዋል፡፡ እንዲሁም፣ እንደ ኤስ.ኦ.ኤስ ሳሕል እና ኢምፓክት በመሳሰሉት ሌሎች ሲቪል ማኅበረሰብ ደርጅቶችም በቦርድ አባልነት አገልግለዋል ፡፡፡
ወ/ሪት ብዙወርቅ፣ በተለያዩ አገሮች በተዘጋጁ ልዩ ልዩ ሞያዊ ሥልጠናዎች ላይ በመሳተፍ ክህሎቶችን በከፍተኛ ደረጃ አዳብረዋል፡፡ ከ1976 ዓ.ም. ጀምሮ አገራቸውን በተለያዩ ደረጃዎች ያገለገሉት ወ/ሪት ብዙወርቅ፥ የአማርኛ፣ የእንግሊዝኛ፣ የፈረንሳይኛ እና የስፓኒሽ ቋንቋዎችን ይናገራሉ፡፡