አበራ ደገፋ (ዶ/ር)
አበራ ደገፋ (ዶ/ር)
ዶ/ር አበራ ደገፋ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ በህግ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩት በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በሶሻል ወርክ እና ሶሻል ዴቨሎፕመንት ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በተጨማሪም፣ በኔዘርላንድስ ከሚገኘዉ ኢንስቲትዩት ፎር ሶሻል ስተዲስ፣ በዓለም አቀፍ ህግ እና ልማት የድኅረ ምረቃ ( post doctoral fellowship) ዲፕሎማ አላቸው፡፡ በኮፐንሃገን እና በፕሪቶርያ ዩኒቨርሲቲ በሚገኙ የሰብአዊ መብቶች ማዕከላት፣ የአጭር ጊዜ የምርምር እና የድህረ-ዶክትሬት ፌሎውሺፕ ትምህርት ቆይታም አድርገዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመደበኛው የመምህርነት ሥራቸው ባሻገር በልዩ ልዩ ከፍተኛ ኃላፊነቶች በሞያቸው ያገለገሉት ዶ/ር አበራ፥ በዘመን ባንክ፣ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠበቆች አስተዳደር ጉባኤ እና በኦሮሚያ የህግ ጆርናል የቦርድ አባል በመሆን መስራታቸው ይጠቀሳል፡፡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባል ሆነው በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከመሾማቸው በፊት፣ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህግ እና የፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ እንዲሁም በኢፌዴሪ የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን በአባልነት አገልግለዋል፡፡
ዶ/ር አበራ፣ በርካታ የኅብረተሰብ ሳይንስ እና የህግ የምርምር ጽሑፎችን በልዩ ልዩ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የኅትመት ውጤቶች ላይ ያሳተሙ ምሁር ናቸው፡፡ የሚበዙት ምርምሮቻቸው እና ጽሑፎቻቸው የሚያተኩሩት፥ በህገ መንግሥት ጉዳዮች፣ በፌዴራሊዝም፣ በኅዳጣን መብቶች፣ የቋንቋ መብቶች እና መሰል ዘርፎች ላይ ነው፡፡
የህግ ምሁሩ ዶ/ር አበራ፥ በዴንማርክ፣ ቤልጅየም፣ ኔዘርላንድስ፣ ናይጄሪያ፣ ግሪክ እንዲሁም በሌሎች አገሮች እና በአገራችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተዘጋጁ ልዩ ልዩ ኮንፍረንሶች እና ወርክሾፓች ላይ የምርምር ስራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ በማስተማር ስራቸው ወቅት የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በማስተማር ባሳዩት የላቀ አፈጻጸም፣ በ2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የሚሰጠውን “የላቀ የማስተማር አበርክቶ” ሽልማት ለማግኘት በቅተዋል፡፡