ብርቱካን ሚደቅሳ


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሊቀ መንበር ብርቱካን ሚደቅሳ፥ በ1966 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቁ በኋላ፣ የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው ሠርተዋል፡፡ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ አካል በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ ጣልቃ በመግባቱ ሳቢያ የፍትሕ ዘርፉን ለቀው፥ በ1997 ዓ.ም. የፓርቲ ፖሊቲካውን እንቅስቃሴ በመቀላቀል የመጀመሪያዋ ሴት የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ሆኑ። በግንቦት 1997 ዓ.ም. በተደረገው ብሔራዊ ምርጫ፣ በወይዘሪት ብርቱካን የተመራው ፓርቲ፣ ብዛት ያላቸውን የፓርላማ ወንበሮች ማሸነፉን ተከትሎ በተነሣ ውዝግብ ሳቢያ ለእስር ተዳረጉ። በ1999 ዓ.ም. የዕድሜ ልክ እስር ተፈረደባቸው።

ከእስር ከተፈቱ በኋላ በስደት በቆዩበት አሜሪካ፣ የናሽናል ኢንዶውመንት የዴሞክራሲ ፌሎው ነበሩ። የ“ስኮላርስ አት ሪስክ” ፕሮግራም የምርምር ፌሎው በነበሩበት በሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ፣ ዓበይት በሆኑ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተግዳሮቶች ላይ ጥናት አድርገዋል። ከሰባት ዓመታት ስደት በኋላ በ2011 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን እንዲመሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃለ መሐላ ፈጽመዋል። በአሁኑ ወቅት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በሊቀ መንበርነት እየመሩ ይገኛሉ።

ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ከአገኙት የመጀመሪያ ዲግሪ ባሻገር፣ ከሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የኬኔዲ “ስኩል ኦቭ ገቨርመንት” በሕዝብ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል።