ውብሸት አየለ


አቶ ውብሸት አየለ፣ በ1947 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱ ሲሆን፣ በ1980 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ በፍትሕ ሚኒስቴር እና በልዩ ልዩ መሥሪያ ቤቶች በህግ ሞያቸው በከፍተኛ አማካሪነት ሠርተዋል፤ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም በዳኝነት አገልግለዋል፡፡ ከዳኝነት ሥራቸው ለቀው የራሳቸውን ቢሮ በመክፈት የህግ አማካሪ እና ጠበቃ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር በሚገኘው የጠበቆች አስተዳደር የሥነ ምግባር ጉባኤ፣ የጠበቆች ማኅበርን በመወከል የኮሚቴ አባል ሆነው ሠርተዋል፡፡

አቶ ውብሸት፣ በአገራችን የመጀመሪያው የሆነው፣ የማስማማትና የግልግል ዳኝነት ማዕከል መሥራች ናቸው፤ ማዕከሉን በዋና ጸሐፊነት አገልግለዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን፣ የእርማት ጊዜያቸውን የጨረሱ ሕፃናት እና ወጣቶች ጥፋተኞች ማገገሚያ ማዕከልን በማቋቋም፣ መሥራች እና አስተዳዳሪ ሆነው ማኅበረሰቡን አገልግለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ራሱን በአዲስ መልክ ማደራጀት ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ ቦርዱን በማማከር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ውይይት በማስተባበር እንዲሁም በሌሎች የቦርዱ እንቅስቃሴዎች ላይ በሞያቸው ከፍተኛ ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ የምርጫ ቦርድ አባል ሆነው እስከተሾሙበት ጊዜ ድረስም፣ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሥር በሚገኘው የፍርድ ቤቶች ማሻሻያ አማካሪ ጉባኤ ሰብሳቢ በመሆን አገልግለዋል፡፡    

አቶ ውብሸት በሞያዊ ሥራቸው ሳይወሰኑ፣ በሲቪክ ማኅበራት እና ማኅበረሰባዊ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ተሳትፎ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ለዚህም፥ የዓለማየሁ ኀይሌ ፋውንዴሽን፣ የፓን አፍሪካ የህግ ባለሞያዎች ኅብረት፣ ኢትዮ ፓረንትስ ትምህርት ቤት የወላጆች ማኅበር፣ ካንሰር አሶሲዮሽንና የተለያዩ ማኅበራት አባል፣ መሥራች እና አስተባባሪ መሆናቸው በአስረጅነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡