የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተቋማዊ ለውጥን ካስተዋወቀበት ከታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም. አንስቶ በርካታ ማሻሻያዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ የማሻሻያ ሥራዎቹ ዋና ዓላማ ቦርዱን በህዝብ ተአማኒ የሆነ ተቋም በማድረግ ለመጪው ምርጫ ማዘጋጀት ሲሆን ከስር የተዘረዘሩት ክንዋኔዎች ቦርዱ አትኩሮት ሰጥቶ የሠራባቸውና እና እየሠራባቸው ከሚገኙት መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የህግ ማእቀፎች ማሻሻል

ቦርዱ በኃላፊነት የሚያስፈጽማቸውን ተግባራት ሲገዙ የነበሩ ዋና ዋና ሦስት ህጎች (የምርጫ ህግ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ህግ እና ፓለቲካ ፓርቲዎች ሥነ ምግባር ህግ) ከዚህ በፊት ቅሬታ ሲቀርብባቸው የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግና ፍትህ ማሻሻያ ጉባኤ ስር ከተደራጀው የዴሞክራሲ ተቋማት የሥራ ቡድን ጋር በጋራ በመሥራት የምርጫ ቦርዱን መልሶ የሚያቋቁም አዋጅ ተረቅቆ በተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ ተደርጓል፡፡ በዚሁ መሠረት ቦርዱ በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 መሠረት እንደገና ተዋቅሯል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከላይ በተጠቀሱት ህጎች ላይ በተደረገ ጥናት መሠረት አድርጎ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ተረቆ ለውይይት ቀርቦ በ2011 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል፡፡  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በድጋሚ ያቋቋመው አዋጅ 1133/2011 ካስተዋወቃቸው የቦርዱ መዋቅራዊ ማሻሻያዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ፦  

  • የቦርዱ አባላት ቁጥር ከዘጠኝ ወደ አምስት ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡
  • የቦርድ አባላት ከዚህ በፊት ከነበረው (ለውሳኔ ብቻ የሚሰበሰብ ቦርድ) በተለየ የሙሉ ጊዜ ሠራተኞች ሆነዋል፡፡
  • የቦርዱ ጽህፈት ቤት ከዚህ እንደቀደመው በፓርላማው ሳይሆን በቦርዱ አማካኝነት የሚደራጅ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የጽህፈት ቤት ኃላፊውም ተጠሪነቱ ለቦርዱ ሰብሳቢ ሆኗል፡፡ 
  • እጩ የቦርድ አባላት አቀራረብ በተሻለ ግልጽነት እና አሳታፊነት እንዲካሄድ ግልጽ መስፈርቶች እና አሠራሮች አስተዋውቋል፡፡ 

በተጨማሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የሥነ ምግባር ህጎች እንዲሁም በቀድሞው የምርጫ ህግ ስር የነበሩ የምርጫ አፈጻጸም እና አስፈጻሚ አካላትን የሚመለከቱ አንቀጾች በአንድ ተጠቃለው አንድ የምርጫ ህግ ሆነው አዋጅ 1162/2011 በመሆን ተዘጋጅተዋል፡፡ የባለሞያዎቹ ቡድን ባቀረበው ሃሳብ መሠረት የተለያዩ አዋጆች ላይ የነበሩት ምርጫን የሚመለከቱ የህግ ማእቀፎች በአንድ የተጠቃለለ የምርጫ ህግ ስር ተጠቃለው የተረቀቁ ሲሆን አዋጁ ላይ ከባለድርሻ አካላት በተለይ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተለያዩ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ ከውይይቶቹ በተጨማሪም በብዙሃን መገናኛዎች እንዲሁም የተወካዮች ምክር ቤት በጠራው ህዝባዊ ውይይት ላይ ክርክሮች የተከናወኑ ሲሆን ህጉ በነሐሴ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. በተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል፡፡

ህጉ ከጸደቀ በኋላ ምርጫ ቦርድ የህግ ክፍል ከሚጠበቁት 39 መመሪያዎች መካከል 22ቱ ተረቅቀው ለውይይት የቀረቡ ሲሆን ሲቪል ማህበራት፣ ሚዲያዎች እና የፓለቲካ ፓርቲዎች ውይይት አድርገውባቸዋል፣ ግብአትም ሰጥተዋል፡፡ ግብአቱን በማካተት ቦርዱ እነዚህን መመሪያዎች አጽድቆ በሥራ ላይ የሚያውል ይሆናል፡፡ ቦርዱ በአዲስ መልክ ከተቋቋመ አንስቶ ሦስት መመሪያዎች ጸድቀው እየተተገበሩ ሲሆን እነሱም የቦርዱ መዋቅር ማሻሻያ፣ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ አፈጻጸም መመሪያ  እና የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ መመሪያ ናቸው፡፡ መመሪያዎቹ ላይ የተወሰዱት ግብአቶች ተጠቃለው በቦርዱ ሲጸድቁ ለህዝብ ይፋ የሚሆኑ ይሆናል፡፡

ህጉ ከጸደቀ በኋላ የምርጫ ቦርድ የህግ ባለሞያዎች አዋጁን ለማስፈጸም ከሚያስፈልጉት 39 መመሪያዎች መካከል 22ቱ ተረቅቀው የተጠናቀቁ ሲሆን 12ቱ መመሪያዎች ለውይይት ቀርበው ሲቪል ማህበራት፣ ሚዲያዎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት አድርገውባቸዋል፣ ግብአትም ሰጥተዋል፡፡ ግብአቱን በማካተት ቦርዱ እነዚህን መመሪያዎች አጽድቆ በሥራ ላይ ለማዋል ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡ ቦርዱ በአዲስ መልክ ከተቋቋመ አንስቶ አራት መመሪያዎች ጸድቀው እየተተገበሩ ሲሆን እነሱም የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ የክልል ጽ/ቤት ኃላፊዎች የምልመላ መመሪያ”፣ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ አፈጻጸም መመሪያ፣  የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ መመሪያ እና የመራጮች ትምህርት ፍቃድ አሰጣጥና ሥነ ምግባር መመሪያ ናቸው፡፡

የቦርዱ አቅም ግንባታ ሥራዎች  

አዲስ በጸደቀው አዋጅ መሠረት ቦርዱ ተጨማሪ አራት የቦርድ አመራር አባላት የተሾሙለት ሲሆን የቦርድ አመራር አባላት ከሰኔ 2011 ዓ.ም. ጀምረው በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ የቦርድ አመራር አባላት የሙሉ ጊዜ የሥራ ክፍሎችን ተከፋፍፈለው በመምራት ላይ የሚገኙ ሲሆን ቦርዱ የክልል ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችን ምልመላም አጠናቅቆ ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ የክልል ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ምልመላ አሳታፊ በሆነ መልኩ የተከናወነ ሲሆን ጥሪው በሚዲያዎች ይፋ ከሆነ በኋላ በቦርድ አመራሮች አማካኝነት መረጣ እና ቃለመጠይቆች ተከናውነዋል፡፡ በኃላፊነት የታጩ ኃላፊዎች ስም ዝርዝርም በየክልሎቹ ለሚንቀሳቀሱት የፓለቲካ ፓርቲዎች ተልኮ አስተያየታቸውን እንዲሰጡበት ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክልልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የቦርዱ ቢሮዎች እንደአዲስ የተደራጁ ሲሆን ቦርዱ ከክልል በታች ያሉ የሥራ ቢሮዎችን በምርጫ ወቅት እንደ አስፈላጊነቱ የሚያደራጅ ይሆናል፡፡      

ምርጫ ቦርድ ከኢትዮጵያ ማኔጅመንት ኢንስቲቲዩት ጋር በመተባበር የሰው ኃይል አስተዳደር የማሻሻያ ፓሊሲ ጥናት እንዲከናወን ያደረገ ሲሆን፣ የጥናቱን ተግባራዊነት ለማረጋገጥ የሰው ኃይል ፓሊሲ አማካሪ በመቅጠር ሙሉ ለሙሉ የተቀየረውን የሰው ኃይል አስተዳደር በፓሊሲ ሰነድ መልክ አዘጋጅቶ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡   

የፓለቲካ ፓርቲዎች

የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ድጋፍ

የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍና ቁጥጥር ከቦርዱ ዋና ዋና ኃላፊነቶች አንዱ ነው፡፡ ቦርዱ ለሁሉም አዲስ ለሚደራጁ ፓርቲዎች የመደራጀት ሥራቸውን ለማከናወን የሚረዳቸው በፕሮግራም እና ህገ ደንብ ዝግጅት ወቅት የሚያስፈልጉ ድጋፎችን፣ ለሥራቸው መፋጠን የሚረዱ የድጋፍ ደብዳቤ የሚሰጥ ሲሆን የምዝገባ ድጋፍ መስጠት እንዲሁም ቅሬታዎችን ሰምቶ የመፍታት ሥራዎችን አብሮ እያከናወነ ይገኛል፡፡

በቀድሞ ህግ በቦርዱ ሰርተፍኬት ያገኙ 84 (35 አገር አቀፍ እና 50 ክልላዊ) እና በመመዝገብ በሂደት ላይ ያሉ 21 (6 አገር አቀፍ እና 15 ክልላዊ) ፓርቲዎች ምዝገባን ከአዲሱ የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግ ጋር ለማጣጣም ለሁሉም ፓርቲዎች ማሟላት የሚገባቸው አሟልተው እንዲያቀርቡ ጥሪ አድርጓል፡፡  

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ድንጋጌዎች እና አዋጁን ለማስፈጸም ቦርዱ በአዋጁ ባወጣው መመሪያ ቁጥር 3 መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሰነድ በመመርመር ማሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች እንዲለዩ እንዲሁም አዋጁ እና መመሪያው ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡

በዚሁ መሠረት፡-

  • አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ወይም በይፋዊ የህዝብ ቆጠራ ውጤት ከ10,000 - 100,000 ብዛት እንዳላቸው የተረጋገጠ ማህበረሰቦችን ለመወከል ከተቋቋሙ ፓርቲዎች ውጭ የሚገኙት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕጉ መሠረት ማሟላት የሚገባቸውን የመሥራች አባላት ብዛት እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ አሟልተው እንዲያቀርቡ፣
  • ጠቅላላ ጉባኤ በወቅቱ ያላካሄዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህጉ በተቀመጠው የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ብዛት መሠረት እንዲሁም አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ወይም በይፋዊ የህዝብ ቆጠራ ውጤት ከ10,000 - 100,000 ብዛት እንዳላቸው የተረጋገጠ ማህበረሰቦችን ለመወከል ከተቋቋሙ ፓርቲዎች በመተዳደሪያ ደንባቸው ላይ በተቀመጠው ብዛት መሠረት እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ በመተዳደሪያ ደንባቸው ላይ ማስተካከያ በማድረግ እንዲያቀርቡ፣
  • በ2002 ዓ.ም. እና በ2007 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ከመንግሥት የተሰጣቸውን ድጋፍ አስመልክቶ በኦዲተር የተረጋገጠ ወቅታዊ የሂሳብ ሪፖርት እንዲያቀርቡ፣
  • ጠቅላላ ጉባኤ የሚያካሂዱበት ጊዜ ያላለፈ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ጉባኤ በማካሄድ በመተዳደሪያ ደንባቸው ላይ ማስተካከያ በማድረግ እንዲያቀርቡ ተገልፆላቸዋል፡፡

በዚሁ መሠረት እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ቀድሞ ከነበሩ 105 የፖለቲካ ፓርቲዎች 76 የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰነዶችን ያቀረቡ ሲሆን በህጉ መሠረት ተሟልቶ የቀረበ ስለመሆኑ እየተመረመረ ይገኛል፡፡

ከላይ ከተጠቀሰው ምርመራ በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህጉ መሠረት ማሟላት የሚገባቸውን የመሥራች አባላት ብዛት ትክክለኛነትን ለመፈተሽ ፖለቲካ ፓርቲዎች ካቀረቡት የመሥራች አባላት ዝርዝር ናሙና የማውጣት ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን ናሙናው ላይ ተግባራዊ ማጣራት እየተደረገ ይገኛል፡፡  ቦርዱ በጊዜ ገደቡ መሠረት የፓርቲ ምዝገባ ሰነዶችን ማሟላት ያልቻሉ ፓርቲዎችን እና የጊዜ ገደቡ እንዲራዘምላቸው የጠየቁ ፓርቲዎች አሳማኝ ምክንያት ባለማቅረባቸው ሰርተፍኬታቸው አንዲሰረዝ ተወስኗል፡፡  ሁለት ፓርቲዎች ብቻ አሳማኝ ምክንያት በማቅረባቸው ሰነድ የሚያቀርቡበት ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው ተወስኗል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ 30 ፓርቲዎች በአዲሱ ህግ መሠረት ጊዜያዊ እውቅና ወስደው ለመመዝገብ ዝግጅቶችን እያከናወኑ ነው፡፡  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከጥር ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ከ35 በላይ የሆኑ የተለያዩ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ውይይቶችን አካሂዷል፣ አስተባብሯል፡፡ እነዚህም ውይይቶች ህጎች ላይ፣ መመሪያዎች ላይ፣ ፓለቲካ ፓርቲዎችን የሚመለከቱ የቦርዱ ውሳኔዎች ላይ እንዲሁም ሚዲያ አጠቃቀም፣ ሲቪክ ማህበራት እና የምርጫ የጊዜ ሰሌዳን የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ የተደረጉ ሲሆን ቦርዱ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበርም ፓርቲዎች ሥልጠና እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና የውይይት መድረክ ምስረታ

ቦርዱ ፓርቲዎች እርስ በርሳቸው ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ቋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይት መድረክ (Political Parties Dialogue Forum) እንዲኖር አስተባብሯል፡፡ በቦርዱ አስተባባሪነት የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ ውይይቶችን ያደረጉ ሲሆን፦

  • የፓርቲዎች ውይይት መድረክ የሚመራበት የሥነ ሥርዓት ደንብ (Rules of Engagement) በጋራ አጽድቀዋል፡፡
  • ፓርቲዎች በጋራና በተናጠል ያላቸውን ግንኙነት እንዲሁም የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸውን የሚገዛ የጋራ ሥነ ምግባር የቃል ኪዳን ሰነድ ፈርመዋል፡፡
  • ፓርቲዎች የጋራ የቃልኪዳን ሰነዳቸውን የሚያስፈጽሙበት እና ክትትል የሚያደርጉበት ምክር ቤት መስርተው አመራሮችን ለሁለት ዙር መርጠዋል፡፡
  • ፓርቲዎች ልንወያይባቸው ይገባል ያሏቸውን አገራዊ ጉዳዮች ለይተው አጀንዳዎቹ ለውይይት የሚቀርቡበት ቅደም ተከተል ላይ ተስማምተዋል፤ በገለልተኝነት ያወያዩናል ያሏዋቸውን ግለሰቦችንም በስምምነት መርጠዋል፡፡
  • ቦርዱ የቴክኒክ እና የማስተባበር እንዲሁም ለውይይት የሚያስፈልጉ ሌሎች ድጋፎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ 

ከሲቪል ማህበራት ጋር በጋራ የሚሠሩ ሥራዎች 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በህግ ከተሰጡት ዋና ዋና ኃላፊነቶች አንዱ የመራጮች እና የሥነ ዜጋ ትምህርት መስጠት እንዲሁም መራጮች መረጃ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ኃላፊነት ከሲቪል ማህበራት ጋር በአጋርነት ለመሥራት የተለያዩ ዝግጅቶች ተደርገዋል፡፡

በዚህም መሠረት የመራጮችና የሥነ ዜጋ ትምህርት ከዚህ በፊት የነበሩበት ችግሮች እንዲታረሙ ተደርገው ህግንና ዴሞክራሲያዊ መርሆች ላይ መሠረት አድርጎ በአዲስ መልኩ ተረቅቆ ከሲቪል ማህበራት ጋር ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ከሲቪል ማህበራት የተገኘው ግብአት ተካትቶ ማንዋሉ የጸደቀ ሲሆን አገር አቀፍ የመራጮችና የሥነ ዜጋ ትምህርት ሥርዓት በመዘርጋት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የመራጮችን ትምህርት አሰጣጥ እና ሥነ ምግባር መመሪያን አስመልክቶ ከሲቪል ማህበራት ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን መመሪያውም ግብአቶቹን በማካተት በቦርዱ ጸድቋል፡፡

ሲቪል ማህበራት ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በተከናወነው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ላይ በታዛቢነት ተገኝተው የትዝብት ሪፓርታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ቦርዱም ይህንን ሥራ ካስተባበረው “የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህብረት ለምርጫ” ከተሰኘ ትብብር ጋር ውይይቶችን አከናውኗል፣ የሰጡትንም ግብአት ለሥራው መሻሻል ተጠቅሞበታል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሲቪል ማህበራት በምርጫ ሥራው ውስጥ ያላቸውን ሚና ለማበረታታት ከማህበራቱ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን ያደረገ ሲሆን የመራጮች ትምህርት እና ምርጫ መታዘብ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ሲቪል ማህበራት ቦርዱ በሚያዘጋጃቸው ውይይቶችና የምርጫ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚመክሩ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

ዓለም አቀፍ ትብብር

ምርጫ ቦርድ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና አጋሮች ጋር ተባብሮ መሥራቱን የቀጠለ ሲሆን ከአጋር ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙነት መሠረታዊ መርሆ የቦርዱ ውሳኔ አሰጣጥ፣ እቅድ እንዲሁም አተገባበር ሥልጣንን ያከበረ ሲሆን የሚያገኛቸው ድጋፎችም በቦርዱ ጥያቄ ላይ ብቻ የተመሠረቱ ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ምርጫ ቦርድንና መጪውን ምርጫን የሚግፉበትን መንገድ ላይ ውይይቶቸ ተደርገዋል፣ ስምምነቶችም ተፈርመዋል፡፡ ዋና ዋና ድጋፍ ሰጪ አጋሮች የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም፣ የአሜሪካን መንግሥት የልማት ተራድኦ እና የአውሮፓ ህብረት ናቸው፡፡

ለአጠቃላይ ምርጫ የተደረጉ ዝግጅቶች እና ኮቪድ19

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለአጠቃላይ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ በማድረግ ዝግጅቶች እያከናወነ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለአጠቃላይ ምርጫ ዝግጅት ከተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎች መካከል፦

  • ለመራጮች ምዝገባ እና ለድምፅ መስጫ ቀን የሚውሉ ዋና ዋና ቁሳቁሶች እና ህትመቶች (የመራጮች መዝገብ፣ የምዝገባ መታወቂያ፣ የጽህፈት መሳሪያ) ግዥ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም በኩል ተከናውኗል፡፡
  • የምርጫ ክልሎች ካርታ ለመጀመሪያ ጊዜ በዲጂታል መልኩ ተዘጋጅቶ ይፋ ሆኗል፡፡
  • ምርጫ ጣቢያዎች ያሉበትን ሁኔታ የማጣራትና በጂፒኤስ ቴክኖሎጂ የመሰብሰብ ሥራ ተከናውኗል፡፡ የምርጫ ጣቢያዎች ዝርዝርም ተዘጋጅቷል፡፡
  • ምርጫ ኦፕሬሽን እና ለመራጮች ትምህርት የሚያገለግሉ ህትመቶች ዝግጅት ተጠናቋል፡፡

የኮቪድ19 ወረርሽኝን ተከትሎ ቦርዱ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ንግግር ያደረገ ሲሆን ወረርሽኙ በምርጫ ሥራ ላይ ሊያስከትለው የሚችለውን ተጽእኖ አስመልክቶ የዳሰሳ ጥናት ካከናወነ በኋላ የምርጫ ዝግጅት ሥራዎችን በማቆም የጊዜ ሰሌዳውን ሰርዟል፡፡ ቦርዱ ወረርሺኙ እንዳለፈ ሁኔታዎችን በመገምገም አዲስ ኦፕሬሽን እቅድና የጊዜ ሰሌዳ ይፋ የሚያደርግ ይሆናል፡፡