ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ
ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ
ሜላትወርቅ ኃይሉ በተለያዩ የመንግሥትና የግል መሥሪያ ቤቶች ከ30 ዓመታት በላይ በማገልገል ልምድ ያላቸው ሲሆን፤ ከባለሞያነት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ አመራርነት ሠርተዋል። የሕዝብ አገልግሎት ተቋማትን /Public Sectors/ ከመቀላቀላቸው በፊት ከ12 ዓመታት በላይ የሕግ ቢሮ በመምራት ለተለያዩ ዓለም ዐቀፍ እና ሀገር ዐቀፍ ድርጅቶችና የቢዝነስ ተቋማት በሕግ አማካሪነትና ሕግን የተመለከቱ ሙያዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ሠርተዋል።
ከዩኒቨርስቲ እንደተመረቁ ባሉት የመጀመሪያ ዓመታት ሜላትወርቅ በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች በሕግ ማስከበር መምሪያ፣ በኦፕሬሽንስ መምሪያ እና በፍትሐ-ብሔር ጉዳዩች ሥራ ክፍል በኃላፊነት ሠርተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ከመሾማቸው በፊት ድርጅቱን ለሁለት ዓመታት በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ያገለገሉ ሲሆን፤ በ2013 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫም ወሣኝ ሚና ተጫውተዋል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ/ Law / የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከሰላምና ደኅንነት ጥናት ኢንስቲትዩት ደግሞ በሰላምና ደኅንነት /Peace and Security/ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፤ በተጨማሪም ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሕዝብ አስተዳደር /Public Administration/ ሁለተኛ ዲግሪ ተቀብለዋል።