Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ክለሳ መድረክ አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 03 ቀን 2017 ዓ.ም የ2016 ዓ.ም. በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የቦርዱ አምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ዝርዝር አፈፃፀምና የ2017 ዓ.ም. በጀት ዓመት ዕቅድ ክለሳ እንዲሁም የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ቀሪና ድጋሚ ምርጫ ላይ የተገኙ ልምዶች የተቀመሩበት መድረክ አካሄደ። የቦርዱ አመራር አባላት፣ በዋናው መሥሪያ ቤቱ የሚገኙ የቦርዱ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች፣ የቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ በቀሪና በድጋሚ ምርጫ ላይ የክትትል ቡድን አባላት የነበሩ የቦርዱ ባለሞያዎች እንዲሁም ሌሎች የዋና መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች የተሣተፉበትን መድረክ በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ይኽን ስድስት ቀን የሚወስደውን መድረክ ከተጠናቀቀው በጀት ዓመት ግምገማና ከተያዘው በጀት ዓመት የዕቅድ ክለሳነት ባሻገር እርስ በርስ በደንብ ለመተዋወቂያና መተማመንን ለማጎልበት እንዲሁም የአመራር ብቃታችን እንዴት እንደሚዳብር በነፃነትና በዕውቀት የምንወያይበትና አቅጣጫ የምናስቀምጥበት መሆን እንደሚገባው በአጽንዖት ተናግረዋል።

በመድረኩ የቦርዱን የ2017 ዓ.ም. በጀት ዓመት ዕቅድን ከቦርዱ አምስት ዓመት የስትራቴጂያዊ ዕቅድ አንጻር የተገመገመና የዕቅዱም የክትትልና የግምገማ ሥርዓት የተዋወቀ ሲሆን፤ በተጨማሪም በሰኔ 2016 የተደረገው የ6ኛው የጠቅላላ ምርጫው ቀሪና ድጋሚ ምርጫ ላይ የተወሰዱ መልካም ተሞክሮችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ተተችተውበታል። የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድም በ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ላይ ከተስተዋሉ ክፍተቶችና ተገማች ከሆኑ ተግዳሮቶች አንጻር ከአስፈጻሚዎቹ የቦርዱ የሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ከክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች ጋር በመገምገምገም የመፍትሔ አቅጣጫ ተሰጥቶባቸዋል።

ስድስት ቀን የወሰደውን የግምገማና የክለሳ፤ እንዲሁም የመማማሪያ መድረክን በንግግር የዘጉት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሲሆን፤ በንግግራቸውም ወርክ ሾፑ (መድረኩ) እንዲሳካ የላቀ ሚና ለነበራቸው የአዘጋጅ አስተባበሪ ኮሜቴ አባላት እና መድረኩን ስፖንሰር ላደረገውን የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP)ከፍተኛ አድናቆታቸውን እና ምስጋናቸውን ገልጸው፤ ቦርዱ ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ የሚደረጉ ጥረቶች በአንድ ጀምበር የምናሳካው ባይሆንም በመድረኩ ግን ለረጅሙ ጉዞ የሚሆን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ግብዓት መሰብሰቡንና ተስፋ ሰጪ ውይይት በመድረኩ ላይ እንደነበር ተናግረዋል።

Share this post