Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የወጣቶች የክርክር መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ አካሔደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወጣቶች በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ሀገራዊ ኃላፊነት ጉዳዩች ዙሪያ በዕዉቀት የተደገፈ መረጃ እንዲኖራቸዉ በማስቻል ረገድ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ሴፍ ላይት ኢኒሼቲቭ ከተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር የወጣቶች የማጠቃለያ የክርክር መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ አካሒዷል፡፡

ክርክሩ በሴፍ ላይት ኢኒሼቲቭ ዋና መስሪያ ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ዉስጥ የተካሄደ ሲሆን ቀደም ሲል በጅማ እና ቢሾፍቱ ከተሞች ላይ ሲካሔድ ለቆየዉ የክርክር መድረክ ማጠቃለያ ፕሮግራም ነዉ፡፡ ክርክሩ የተካሔደዉ በዩኒቨርሲቲ እና በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል ሲሆን ‘የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢኮኖሚ ፖሊሲ እና ከትምህርት ፖሊሲ የትኛዉ ላይ ትኩረት ቢያደርጉ በህዝቡ ተመራጭ ያደርጋቸዋል?’ በሚል ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ነዉ፡፡

በዚህ ማጠቃለያ መድረክ ላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስነ-ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ክፍል ባልደረቦችን ጨምሮ ከአዲስ አበባ እና ከቢሾፍቱ ከተሞች የተዉጣጡ ወጣቶች፣ የሲቪል ማህበሰብ ድርጅቶች ባለሰልጣን ተወካዮች እና ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተሳትፈዋል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስነ-ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ክፍል ባልደረቦች በበኩላቸዉ ቦርዱ ይህን መሰል መድረኮች ሲያዘጋጅ ወጣቶች በሀገራቸዉ ጉዳዮች ላይ እና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የሚኖራቸዉ አስተዋፆ ከፍተኛ መሆኑን በማመን ነዉ ብለዋል፡፡ በመሆኑም ቦርዱ ይህን መሰል የወጣቶች ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን ለወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳዉቀዋል፡፡

Share this post