Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሐበጋር ዲቤትስ ጋር በመተባበር በሐረር ከተማ የክርክር መድረኮችን አዘጋጀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዜጎች በመረጃ ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንዲያደርጉ እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሚኖራቸዉን ተሳትፎ ለማጉላት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ቦርዱ ከሐበጋር ዲቤትስ (ደበበ ኃ/ገብርኤል የሕግ ቢሮ) ጋር በመተባበር በሐረር ኤስ ኦ ኤስ እና በሐረር ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተማሪዎች መካከል የክርክር መድረክ አካሄዷል፡፡

የክርክሩ ፍሬ ሀሳቦች በሁለት ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሲሆን እነርሱም፡ ለኢትዮጵያ የሚሻለዉ የፖለቲካ ሥርዓት ፕሬዝዳንታዊ ወይስ ፓርላሜንታዊ እንዲሁም የነፃ ገበያ ሥርዓት ለኢትዮጵያ ዕድገት የተሻለ ሥርዓት ነዉ ወይስ አይደለም? የሚሉ ነበሩ፡፡

በክርክሩ ላይ የየትምህርት ቤቶቹ ርዕሰ መምህራንን ጨምሮ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሐረሪ ክልል ቅ/ጽ/ቤት የስነ-ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ባለሙያ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ፣ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች እና ተማሪዎች ፕሮግራሙን ታድመዋል፡፡ በክርክሩ ላይ የተሳተፉ ተማሪዎችም ሀገራችን አሁን እየተከተለች ያለችውን የፖለቲካ አስተዳደር ሥርዓት ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎች ጋር በማነፃፀር ሰፊ ክርክር ያካሄዱ ሲሆን በተለይም አሁን ሀገራችን እየተከተለች ያለውን የፓርላሜንታዊ ሥርዓት ከፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት የሚለይበትን፤ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አንዱ ከሌላኛው የተሻለ አማራጭ የሚሆንበትን ምክንያቶች በመተንተን ተከራክረዋል። በሌላ በኩል ተማሪዎች በነፃ ገበያ ሥርዓት ዙሪያ ክርክር ያደረጉ ሲሆን ጥቅም እና ጉዳቱን በመዘርዘር እና ከታዳሚዎች በተነሳላቸዉ ጥያቄ መሰረት በጥልቀት ተሟግተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በመወከል የተገኙ ባለሙያዎችም በበኩላቸዉ ቦርዱ እንደነዚህ አይነት የሐሳብ ፍጭቶች እና ዴሞክራሲያዊ የውይይት መድረኮችን በተማሪዎችና በሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል እንዲዘወተሩ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን በመግለፅ በዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳቦች ዙሪያ ግንዛቤን ከማስጨበጥ ባሻገር ወጣቱ ትውልድ የክርክር ባህልን እንዲያሳድግ የሚያግዝ በመሆኑ ለወደፊትም ይህን መሰል መድረኮች ተጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ አሳዉቀዋል፡፡

Share this post