Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ማስተዋወቂያ መድረክ አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ተዓማኒነት ባላቸው ምርጫዎች እና የህዝብ ውሳኔዎች አማካይነት በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን ማጎልበትንና ማፅናትን ዋና ስትራቴጂያዊ ግቡ ያደረገ ከ2016/17 ዓ.ም እስከ -2020/21 ዓ.ም የሚተገበር ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ አደረገ።

ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚተገበረው የስትራቴጂክ ዕቅድ ስድስት አምዶችን (pillars) ማለትም የምርጫ ሕግ ማዕቀፍ፣ የዜጎች ተሳትፎና የግብ ትስስር፣ የምርጫ ሥራዎች፣ የምርጫ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና አጋርነት፣ ተቋማዊ ለውጥና ግንባታ እንዲሁም የምርጫ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራን ማእከል አድርጎ የተዘጋጀ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ በስትራቴጂክ ዕቅድ የማስተዋወቂያ መርሃ ግብር የመክፈቻ ንግግራቸው የዕቅድ ሰነዱ ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን፣ ከ6ኛው ጠቅላላ ሀገር አቀፍ ምርጫ የተገኙ ልምዶችን እና ምክረ ሃሳቦችን ማእከል አድርጎ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

ስትራቴጂክ ዕቅዱ በቀጣይ ለሚደረገው 7ኛው ብሔራዊ ሀገራዊ ምርጫ እና የአካባቢ ምርጫዎች ፍኖተ ካርታ ዝግጅት መሠረት ይጥላል ያሉት ወ/ሮ ሜላትወርቅ በዚህ ስትራቴጂክ ዕቅድ የተቀመጡ ግቦች ሙሉ በሙሉ እንዲሳኩ ከመንግስት የሚጠበቁ አስፈላጊ የሀብት ድጋፎች እንደተጠበቁ ሆኖ፣ ለእቅዱ ስኬታማነት የቦርዱ ሠራተኞች እና ባለድርሻ አካላት ያላሰለሰ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ እና የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት ፣ የዲሞክራሲ ተቋማት፣ የመንግሥት መ/ቤቶች፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኀበራት፣ ፍርድ ቤቶች፣ የሚዲያ ተቋማት አመራሮችና ተወካዮች እንዲሁም ሌሎቾ ጥሪ የተላላፈላቸው እንግዶች ታዳሚ ነበሩ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ አዲስ በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ውጤት ባስመዘገበበት በ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል ይህ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ አይነተኛ መደላድል እንዲሆን በቦርዱ የተዋቀረው የስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅ ኮሚቴ ያዘጋጀው መነሻ በሃሳብ ግብዓት እንዲዳብር በተደጋጋሚ ለምርጫ ቦርድ አመራር አባላት፣ ለቦርዱ ሠራተኞች፤ለፖለቲካ ፓርቲዎች፤ለሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቀርቦ እንዲዳብር ተደርጓል።

ወ/ሮ ሜላትወርቅ በዚህ አመርቂ የዕቅድ ዝግጅት ቀና ተሳትፎና ድጋፍ ለነበራቸው የቦርድ አመራር አባላት፣ ሠራተኞች፣ የስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት ኮሚቴ አባላት፣ ለተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ፣ ለአውሮፓ የምርጫ ድጋፍ ማእከል (ECES) እና ለምርጫ ሥርዓት ዓለም አቀፍ ፋውንዴሽን (IFES) ተቋማት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በተያያዘ ዜና የ6ኛውን ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ በፍ/ቤት የተደረጉ የምርጫ ነክ ክርክሮች ውጤቶችን የያዘ አጭር ቡክሌት /Compendium/ ለታዳሚው የማስተዋወቅ እና ለታዳሚዎች የማሰራጨት ሥራ ጎን ለጎን መሠራቱ ታውቋል።

Share this post