Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4/12 ምክር ቤት ጋር በመተባበር በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና በምርጫ ሂደት ዙሪያ ሥልጠና ሰጠ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4/12 ምክር ቤት በተደረገለት ግብዣ መሰረት የስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ክፍል ከቦርዱ አዲስ አበባ ቅ/ጽ/ቤት እንዲሁም ከምርጫ ኦፐሬሽንስ የሥራ ክፍል ጋር በመቀናጀት ለሕፃናት ፓርላማ አባላትና ለባለድርሻ አካላት በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የዜጎች መብትና ሃላፊነቶች፥ የኢትዮጵያ የምርጫ ሂደትን ከምርጫ ህጉ አኳያ እና በሕፃናት የፓርላማ አሰራር፥ አወቃቀርና መልሶ ማደራጀት ዙሪያ ላይ ያተኮረ የአንድ ቀን ሥልጠና የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ሰጥቷል።

በሥልጠናው ላይ በወረዳው ከሚገኙ 13 ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 100 የሕፃናት ፓርላማ አባላት፥ ከሸገር ከተማ የተጋበዙ እንግዶች፥ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ መምህራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑት ተማሪዎች በዲሞክራሲየዓዊ ሥርዓት ውስጥ መብትና ግዴታዎቻቸውን ጠንቅቀው በማወቅ እንዲሁም ስለሀገራቸው የመንግስት አወቃቀርና የፓርላማ ሥርዓት በቂ ግንዛቤ በማግኘት የምርጫ ተሳትፎን እየተለማመዱ እንዲያድጉ የሚረዳቸውን ሥልጠና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ክፍል እና ከቦርዱ አዲስ አበባ ቅ/ጽ/ቤት በመጡ ባለሙያዎች አማካኝነት የግናዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ ተደርጓል።

የወረዳ 4/12 ምክርቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ካሳሁን ተሾመ በሥልጠናው ወቅት ተማሪዎቹ በቅርቡ ለሚያካሂዱት የሕጻናት ፓርላማ ምርጫ የሚያግዛቸውን ቴክኒካዊ ክህሎት ጨምሮ በምርጫ አስፈላጊነት፤ የዜጎች መብት፥ ኃላፊነትና በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ዙሪያ ግንዛቤ የጨበጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። አፈ -ጉባኤው አያይዘውም ከኢትዮጵያ ብሔራዎ ምርጫ ቦርድ በኩል እንደዚህ አይነቱ ሥልጠናና ድጋፍ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸውን ገልጸው ቦርዱ ላደረገው ሥልጠናና ድጋፍ ምስጋናቸውን አስተላልፈዋል::

Share this post