Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ ፓርቲ ከሀገር ዓቀፍ የፖለቲካ ፓርቲነት እንዲሰረዝ የኢትጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የወሰነውን ውሳኔ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመቀበል የሰጠው ውሳኔ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ በአዋጅ ቁጥር 1162/11 መሰረት በሀገር ዓቀፍ ፓርቲነት ለመመዝገብ ጥያቄ አቅርቦ በአዋጁ አንቀጽ 64 መሰረት ፓርቲው ከአምስት ክልሎች ማቅረብ የሚገባውን አስር ሺህ (10,000) የመስራች አባላት በቁጥር ያቀረበ ቢሆንም የክልላዊ አባላት ስብጥርን በሚመለከት ግን ከአንድ ክልል መሟላት ከሚገባው አንድ ሺህ አምስት መቶ (1,500) መስራች አባላት ውስጥ አንድ ሺህ አርባ አምስት (1,045) መስራች አባላት ብቻ ያቀረበ በመሆኑ ለሀገር ዓቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ የሚያስፈልገውን የመስራች አባላት ክልላዊ ስብጥር አሟልቶ ስላልቀረበ ከየካቲት 29 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ከፖለቲካ ፓርቲነት እንዲሰረዝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወስኖ ነበር፡፡

ፓርቲው ይህን ውሳኔ በመቃወም ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርቦ ፍ/ቤቱም ከየክልሎች ከሚሰበሰበው 15% የመስራች አባላት ቁጥር ውስጥ ቢያንስ 15% የሚሆኑት የክልሉ መደበኛ ነዋሪ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንጂ ከአጠቃላይ ከመሥራች አባላት መካከል 15% የሚሆኑት ከየክልሎቹ ማሟላት አለበት የሚል አይደለም በማለት የቦርዱን ውሳኔ በመሻሩ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትም የከፍተኛ ፍ/ቤቱን ውሳኔ አጽንቶት ነበር።

ቦርዱ ጉዳዩን በይግባኝ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበ ሲሆን ችሎቱም በሰበር መዝገብ ቁጥር 247740 ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ ከፓርቲው አጠቃላይ አባላት ከአንድ ክልል የሚመዘገቡ የመስራች አባላት ቁጥር ከ40% መብለጥ እንደሌለበት፤ ከቀሪዎቹ አራት ክልሎች ግን ከአጠቃላይ በፓርቲው ከተመዘገቡት አባላት መካከል ቢያንስ 15% የሚሆኑት መደበኛ ነዋሪ መሆናቸው መረጋገጥ ያለበት በመሆኑ ፓርቲው ከአንድ ክልል የሚጠበቅበትን ዝቅተኛ የአባላት ቁጥር ባለማሟላቱ ምክንያት ቦርዱ የካቲት 29 ቀን 2014 ዓ.ም ፓርቲው ከምዝገባ እንዲሰረዝ የሰጠው አስተዳደራዊ ውሳኔ ተገቢነት ያለው ነው በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

Share this post