Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጄንሲ አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸው የመግባቢያ ሠነድ ተፈራረሙ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መራጮች በቂ የሆነ የሥነ-ዜጋ እና የምርጫ ነክ ግንዛቤ የሚያገኙበትን ስልት በመቀየስና የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት መስጠት ከዋና ዋና ተግባራቱ መካከል አንዱ ነው፡፡ ቦርዱ የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርትን በቋሚነት ተደራሽ ለማድረግ ይረዳው ዘንድ የተለያዩ የህትመት ውጤቶችን በማዘጋጀት በትምህርት ተቋማት፣ በህዝብ ቤተ-መጻሕፍት፣ በመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ በማስቀመጥ ለዜጎች ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጄንሲ ዜጎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ እና የዳበረ የንባብ ባህል እንዲኖራቸው በተለይ በዲሞክራሲያዊ ዕሳቤዎች፥ በምርጫ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የህትመት ውጤቶችን ለማዳረስና አገልግሎቱን ዘመናዊ በማድረግ ለማሕበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የጋራ መግባቢያ ሠነድ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና በኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ መካከል ተፈርሟል፡፡

የመግባቢያ ሠነዱን ቦርዱን በመወከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ እንዲሁም በኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጄንሲ በኩል ደግሞ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ ፈርመዋል፡፡

ስምምነቱ የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በእኩል ኃላፊነት መርሕ ላይ ተመስርተው ለመሥራት የሚያስችላቸው ከመሆኑም ባሻገር ሁለቱም ተቋማት የስምምነት ሰነዱ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ እና የዳበረ የንባብ ባህል ያለው ትውልድ ለማፍራት እገዛ ያደርጋል ብለው ያምናሉ፡:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ታህሣሥ 23 ቀን 2016 ዓ.ም.

Share this post