የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕገ መንግስቱ እና በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 በተሰጠው ሥልጣን መሰረት የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ የሲቪል ማህበራት ፍቃድ ይሰጣል።

የስነ ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት አስፈላጊነት ዜጎች በምርጫ ለመሳተፍ እና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማድረግ በሚወስኑት ውሳኔ ላይ ተፅዕኖው በግልፅ ይታያል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃም ይህንን ግብ እውን ለማድረግ የሲቪል ማህበረሰብ ተሳትፎም አስፈላጊ ነው።

በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሲቪል ማህበራት ጋር በጠቅላላ የብሔራዊ ምርጫ እና ህዝብ ውሳኔዎች በተካሄዱባቸው ጊዜያት አብሮ በመሥራቱ ለመራጮች መረጃን በተሻለ መልኩ ለማዳረስ የማይናቅ ጠቀሜታ እንዳገኘ እሙን ነው፡፡ ቦርዱ ወደፊት ለሚተገብራቸው ተግባራት ቀደም ብለው አብረውት መሥራት የጀመሩ የሲቪል ማህበራት እና የአዳዲስ ሲቪል ማህበራት ተሳትፎ በዘላቂነት መቀጠል እንዳለበት ስለሚያምን በስነ ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት ላይ የሚሳተፉ የሲቪል ማህበራትን መዝገብ እንደ አዲስ የማደራጀት ሥራ ጀምሯል።

በዚህም መሰረት፡-

  • በሕጋዊ መንገድ በሲቪል ማህበራት ኤጀንሲ የተመዘገባችሁ ፤
  • የማስተማር ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል አቅም ያላችሁ ፤
  • ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ግንኙነት የሌላችሁ (ገለልተኛ የሆናችሁ) ፤
  • በመመሪያው የተቀመጡትን መስፈርቶች የምታሟሉ እና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ከዚህ በፊት በሥነ-ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት በመስጠት ሥትሰሩ የነበራችሁ እና ወደፊት መሥራት የምትፈልጉ የሲቪል ማህበራት በተቀመጠው መመዝገቢያ ቅፅ ላይ የሚያስፈልገውን መረጃ ሞልታችሁ ይህ ማስታወቂያ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ባሉት 10 የስራ ቀናት ውስጥ በምርጫ ቦርድ ዋና መስሪያ ቤት ቢሮ ቁጥር 106 በግንባር ወይም በ votersedu [at] nebe.org.et ኢሜይል አድራሻ ማቅረብ ትችላላችሁ።

አመልካቾች የማመልከቻ ቅጾችን ከታች ካለው ሊንክ፣ ዋና መ/ቤት እና የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ማግኘት ይችላሉ። ለተጨማሪ ማብራሪያ በስልክ ቁጥር 0995003865 በመደወል መጠየቅ ይቻላል፡፡

የማመልከቻ ቅጽ ለማግኘት እዚህ ላይ የጫኑ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ማስታወቂያ
ታህሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም