የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለሙያዎች ዘመናዊ የሪከርድና መረጃ አስተዳደር ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችላቸውን ስልጠና ወሰዱ
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከተለያዩ የሥራ ክፍሎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች በዶክመንቴሽን፣ በሪከርድ እና መረጃ አስተዳደር ርዕሰ ጊዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት በመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች አማካኝነት ከ ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ የቆየ ስልጠና ተሰጥቷል።
አስር ቀን በቆየው ስልጠና በቦርዱ የሥራ ሂደት የሚሰበሰቡ ሪከርዶች ታሪካዊ ፋይዳቸው የላቀ በመሆኑ ሳይንሳዊ በሆነ ዘመናዊ የሪከርዶች አስተዳደር ስርዓት መደራጀት እና መጠበቅ እንዳለባቸው አፅንዖት ተሰጥቶታል፡፡
ስልጠናው በቦርዱ ካሉት ሪከርዶች መካከል ዘላቂ ጠቀሜታ ያላቸውን እና የሌላቸውን በመለየት የሠነዶች ምዘና እና መረጣን ለማካሄድ ሰልጣኞቹን የሚያስችላቸው ሲሆን ወሳኝ የሆኑትን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሪከርዶችና መረጃዎችን ከማንዋል አሠራር ወደ ዲጂታል የመረጃ አስተዳደር ስርዓት ለማሸጋገር ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር ታምኖበታል፡፡
ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ